የአርሶአደሮችን የምርት አቅም ለመጨመር በኩታ ገጠም የማደራጀት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

17

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደን ሽፋንን በአንድ በመቶ ማሳደግ አካባቢው የሚታወቅበትን የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ማስፋት የምዕራብ ጎጃም ዞን የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ትኩረት ነው። የጃቢ ጠህናን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ ሞሴ እንዳሉት ዞኖ ለአትክልት፣ ፍራፍሬ እና ደን ልማት ያለውን ምቹ የአየር ንብረት በመጠቀም በዘመናዊ የክላስተር አሠራር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው።

በወረዳው ከ469 ሺህ በላይ የቡና ችግኞች እና 40 ሺህ የፓፓያ ችግኞች ተዘጋጅቷል። የአቮካዶ ኩታገጠም ልማትም በ100 ሄክታር መሬት ላይ ለመተግበር የጉድጓድ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል። የአቮካዶ ችግኝ አቅርቦት እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት ከዞን እና ከክልል መሪዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራም ይገኛል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን የደን ችግኝ ተዘጋጅቷል። ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል። ለተከላው ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቷል።

የደን ልማቱን ዘላቂ ለማድረግ ስድስት አዳዲስ የተፋሰስ ማኅበራትን በማደራጀት ወደ ሥራ ተገብቷል። የችግኞችን የመጽደቅ ምጣኔ ለማሳደግ በጥራት ዝግጅት፣ በወቅታዊ አረም እና ኩትኳቶ ላይ ትኩረት ተደርጓል። ይህ የሥራ እንቅስቃሴም ከባለሙያው፣ ከመሪው እና ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እና በየደረጃው በሚደረግ ግምገማ እየተመራ ነው ብለዋል።

በደን ልማት፣ በቡና እና በፍራፍሬ ልማት 134 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰውመኾን ተገኘ አስታውቀዋል።

ለተከላ ይውላል የተባለው የመሬት መጠን 14 ሺህ 500 ሄክታር ነው። እስካሁን 43 ሚሊዮን የደን ችግኝ ጉድጓድም ተዘጋጅቷል፤ ይህም የዕቅዱ 33 በመቶ ነው።

በመኸር ወቅት በአጠቃላይ ለመትከል ከታቀደው ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ ነው። ከዚህ ውስጥ 1ነጥብ 2 ሚሊዮኑ የቡና ችግኝ ነው።

አርሶ አደሮች ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አቅም ያላቸው እንዲኾኑ ለማስቻል በክላስተር የማደራጀት ሥራ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል። ለቡና እና ለአቦካዶ ለእያንዳንዱ 100 ሄክታር መሬት ተለይቷል።

ከፍላጎት አኳያ የችግኝ አቅርቦት ክፍተት እንዳይኖር ከክልሉ መንግሥት ጋር የቅርብ ንግግር መኖሩንም አስታውቀዋል።

እንደ አማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 1 ነጥብ 78 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል። ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም ለተከላ ተለይቷል።

#አሚኮ_ዜና #የአረንጓዴ_አሻራ_ምዕራብ_ጎጃም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በመኸር እርሻ ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታገጠም እርሻ የሚለማ ነው።
Next article“ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ መኾን አለባቸው”