
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን የታቀዱ የግብርና ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የዘንድሮው የክረምት እርሻ እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል። የምርጥ ዘር እና የማዳበሪያ ግብዓቶች በወቅቱ እንደቀረቡላቸውም ገልጸዋል።
ማሳቸውን ቀድመው በማለስለስ መሬታቸውን በበቆሎ ሰብል መሸፈን እንደቻሉም ተናግረዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኅላፊ በለጠ ጥጋቡ በምርት ዘመኑ 321 ሺህ 531 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። በምርት ዘመኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 515 ሺህ 510 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መግባቱን ገልጸዋል።
ከገባው ውስጥ ከ190 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሮች በፍትሐዊነት መሠራጨቱን ነው ያስረዱት።
ቀድመው በሚዘሩ የዞኑ አካባቢዎች እስካሁን ከ28 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በመስኖ እና በበልግ ወቅት የተነሱ ሰብሎች ወደ መኸር እርሻ ዝግጅት እንዲሸጋገሩ መደረጉን ገልጸዋል። ለአርሶ አደሮች ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱና በፍትሐዊነት የማሠራጨት ሥራ መከናወኑንም አስታውቀዋል።
በክልል ደረጃ በ2018/19 የምርት ዘመን፦
አርሶ አደሮች ወቅቱን ጠብቀው ማሳቸውን በዘር ከመሸፈን ባለፈ የተዘሩትን ሰብሎች የአረም ቁጥጥር ሥራዎችንም ጎን ለጎን በትኩረት ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
