“የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት የከተማዋ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መሠረት የጣለ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

15
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎችን ከማስዋብ ያለፈ ፋይዳን የያዘ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
‎ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ፣ ከእንጦጦ እስከ ቀበና ባለው መስመር የሚከናወነው መጠነ ሰፊ የከተማ ትራንስፎርሜሽን፤ ከወንዞቹ ባሻገር እስከ 50 ሜትር የሚዘልቅ ነው። የአረንጓዴ ኮሪደሮችን፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን እና የንግድ ቦታዎችን ልማት ያካተተ መኾኑን ገልጸዋል። ከተማዋንም በእጅጉ የቀየረ ነው ብለዋል።
‎የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ልዩ የሚያደርገው ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው ነው። የወንዝ ዳርቻዎችን ገጽታ እና አገልግሎት ከማሻሻል ባለፈ በኮንስትራክሽን፣ በኢንጂነሪንግ፣ በመልክዓ-ምድር ውበት ግንባታ፣ በሎጂስቲክስ እና በተያያዙ ዘርፎች ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
ለሀገር በቀል ተቋራጮች እና አቅራቢዎች ዕድሎችን አመቻችቷል። አብዛኛው ሥራ በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች መቀረጹና መተግበሩ፤ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በከተማ ልማት እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው አቅም እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
‎የልማቱ ዘላቂነትም እኩል ትኩረት የሚሰጠው ነው። ቀደም ሲል መርዛማ ኬሚካሎች እና ቆሻሻዎች የሚጣሉባቸው፣ በወንዝ ዳርቻዎች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ የጎርፍ አደጋ ይጋርጡ የነበሩት እነዚህ አካባቢዎች አሁን ላይ ወደ አረንጓዴ፣ ጤናማ እና ለሕይወት ምቹ ወደኾነ የከተማ ቦታነት እየተቀየሩ ይገኛል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ሁኔታም፤ የንግድ እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ተቀናጅተው መገንባታቸው፤ የአካባቢ ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ከዚህ ቀደም ከነበረው ያልተናበበ ሥራ ተላቀው በጥናት እና በጋራ ግብ ተባብሮ መሥራት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
‎ይህ ፈጣን የልማት ሥራ አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ ይበልጥ የተሳሰረች፣ በኢኮኖሚ ንቁ እና ሰውን ማዕከል ያደረገች ከተማ የማድረግ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ላይ መሠረት የተጣለበት የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleእውቅና ላገኙ የቤት ማኅበራት በቂ ቦታ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበአማራ ክልል በመኸር እርሻ ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታገጠም እርሻ የሚለማ ነው።