እውቅና ላገኙ የቤት ማኅበራት በቂ ቦታ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ።

16

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለብዙዎች መጠለያ ማግኘት እና የቤት ኪራይ ሥጋትን መገላገል የሕይወት ትልቁ ስኬት ነው። ይህንን የዜጎች አንገብጋቢ የቤት መሥሪያ ቦታ ችግር ለመቅረፍ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበር ለተደራጁ ዜጎች የመሥሪያ ቦታ እያዘጋጀ እያስተላለፈ ይገኛል።

ቢሮው በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ለ1ሺህ 800 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አዘጋጅቶ ለመስጠት አቅዶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

ባለፉት ወራት ውስጥ (የግንቦት እና የሰኔ ወር አፈጻጸምን ሳይጨምር) ከ1ሺህ 100 በላይ ለሚኾኑ የቤት ማኅበራት መሬት መተላለፉን በአማራ ክልል መሬት ቢሮ የከተማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን መሪ ገነቱ አቤ ለአሚኮ ተናግረዋል።

ይህም ለመስጠት ከታቀደው 1ሺህ 800 ማኅበራት ውስጥ 62 በመቶው ለሚኾነው ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። እስካሁን ቦታ ለወሰዱ ማኅበራትም 1ሺህ 84 ሄክታር መሬት መተላለፉን ገልጸዋል።

እስካሁን በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ምሥራቅ ጎጃም እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች የሚገኙ በርካታ ማኅበራት የቦታው ባለቤት መኾን ችለዋል ነው ያሉት።

በቀጣይ ባሕር ዳርን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች ሕጋዊ ዕውቅና ላገኙ ማኅበራት መሬት ለማስተላለፍ በቂ የቦታ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁም ተጠቁሟል።

#አሚኮ_ዜና #ትምህርት_ደቡብ_ወሎ #ኮምቦልቻ #አማራ_ክልል # ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleምክር ቤቱ የትምህርት ቤት ምገባን ሀገራዊ ተግባር ለማድረግ ተወያይቶ ረቂቅ አዋጁን ለጤና እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ መራ።