
አዲስ አበባ: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በመሪዎቿ በኩል በካይ ጋዝ የሚለቁ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ገንዘብ ሊከፍሉ ይገባል የሚሉ ክርክሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የዘርፉ ምሁራን ደግሞ የተፈጥሮ ፀጋዋን ካርቦን በመሸጥ ጥቅም ልታገኝ ይገባል የሚሉ ሀሳቦችን ይዘው ሲሞግቱ ሰንብተዋል።
ለዚህ ምላሽ የሚኾን ረቂቅ አዋጅ የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በ23ኛው መደበኛ ጉባኤው መክሮበታል። የአዋጁ መጽደቅ ያደጉ ሀገራት የሚያመነጩት በካይ ጋዝ በራስ አቅም ካሳ ለማግኘት እና የተፈጥሮ ሀብቷን በመሸጥ ጥቅም ለማግኘት ይረዳታል። በውይይቱ ከተጠሪነት፣ ከመመዘኛ እና ከቁጥጥር አንፃር ሐሳቦች ቀርበዋል።
እነዚህን እና ሌሎች ሐሳቦችን አዳብሮ እንዲመለከተው የካርቦን ግብይት ሽያጭ ረቂቅ አዋጅ በሚል ለተጨማሪ ዕይታ ወደ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የፌዴራል ታክስ አሥተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
በተጨማሪም የትምህርት ቤት ምገባን ሀገራዊ ተግባር አድርጎ ለመሥራት እና የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነትን ለማጠናከር የሚያገለግለው የምግብ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅን ለጤና እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ መርቶታል።
#አሚኮ_ዜና #የተወካዮች_ምክር_ቤት #አዋጆችን_ለተጨማሪ_ዕይታ_መምራት #አዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
