
አዲስ አበባ: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ሥብሠባ የተለያዩ አዋጆችን አጽድቋል።
ውይይት ተደርጎባቸው ከጸደቁ አጀንዳዎች መካከል ኢትዮጵያ ከስዋቲኒ፣ ከሴራሊዮን፣ ከባንግላዴሽ እና ከአንጎላ ሀገራት ጋር ያደረገቻቸው የአየር አገልግሎት ስምምነቶች ይጠቀሳሉ።
ስምምነቶቹ የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ያጠናክራሉ፣ የሥራ ዕድልም ይፈጥራሉ። ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥገና እና ሥልጠና የሚሰጥበትን ዕድልም ያሳድጋሉ ነው የተባለው።
እነዚህ ዘርፎች የውጭ ምንዛሬን ለኢትዮጵያ በማስገኘት እና የአየር ደኅንነትን በማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በቬትናም መካከል የተፈረመው የዲፕሎማቲክ እና አገልግሎት ቪዛ የማስቀረት ስምምነት ላይ መክሯል።
ስምምነቱ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዲፕሎማቶች እና ዜጎች በየጊዜው የሚያደርጉትን ጉዞ ለማቀላጠፍ፣ ጊዜ ለመቆጠብ እና የሁለትዮሽ ትብብርን እንደሚያሳድግ ታምኖበታል።
ምክርቤቱ ሌላው የተወያየበት ጉዳይ በኢትዮጵያ እና
በሩሲያ መካከል የተደረገው የባዮሎጅካል የምርምር ማዕከል መቋቋም ነው። በተለይም ኢትዮጵያ በዓሳ እና በእንስሳት ያላትን አቅም ወደ ሀብት ለመቀየር፣ የምርምር አቅምን ለማሳደግ እና ወደ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል።
በተመሳሳይ ዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ በዘርፉ ያለውን የሰው ኀይል አቅም ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን የዘርፉ ምርቶችን ወደ ሩሲያ ለመላክ እንደሚያግዝም ተመላክቷል።
#አሚኮ_ዜና #አዋጆች_መጽደቅ #አዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
