
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብልህ ልጆች ሁልጊዜም እናታቸውን ያስባሉ፤ ጠቢባን በመከራም በፍስሐም ጊዜ ሀገራቸውን ያስቀድማሉ፤ ሁልጊዜም ለሀገራቸው የተሻለውን ያደርጋሉ፤ ራሳቸውን ሰውተው፤ ሀገራቸውን ያጸናሉ። በሀገራቸው ደስታ ይደሰታሉ፤ በሀገራቸው ፈተና ይፈተናሉ፤ በሀገራቸው መከራም ያዝናሉ፤ ለሀገራቸው ችግርም የመፍትሔ ምንጭ ይኾናሉ።
አንድ ቀን ከመወራወር ለዓመታት በሃሳብ መከራከር፤ ለአንድ ቀን ከመዋጋት ለዓመታት መወያየት ይሻላል። የአንድ ቀን ጦርነት ሕይወት ያጠፋል፤ ንብረት ያወድማል፤ ቂም ያስቋጥራል፤ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። ለዓመታት በቆዬ ውይይት ግን ሰዎች አይሞቱም፤ ንብረቶች አይወድሙም፤ ቂም እና ቁርሾም አይኖርም። ከዚህ ይልቅስ ልብ ለልብ መግባባት፤ መስማማት እና አንድነትን ማጽናት ይመረጣል።
ዴሞክራሲን በአንድ ጀምበር ያጸና ሀገር የለም። ዛሬ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ አርዓያ የሚቆጠሩ ሀገራት ዴሞክራሲን ለማጽናት ለዓመታት ሞክረዋል። ከዓመታት በኋላም ፍጹም ባይኾን እንኳን የተሻለ ዴሞክራሲን ገንብተዋል፤ የዴሞክራሲ ተቋማትን አስፍተዋል፤ እዚህ ለመድረስ አያሌ ፈተናዎችን፤ ጎታች እና ወደ ግጭት የሚያስገቡ ሃሳቦችን አልፈዋል።
ስህተቶቻቸውን እያረሙ፤ ግጭትን ተጠይፈው ውይይትን ባያስቀድሙ ኖሮ ዛሬ ከደረሱበት ባልደረሱ ነበር። ሀገር ለመገንባት፤ አንድነቷን፣ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን ለማጽናት ወገብ የሚያጎብጥ ትዕግሥት፤ ነገን የሚያይ አስተዋይነት እና ብልሃት ያስፈልጋል። ሀገር “ጨዋታው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ” በሚል አይነት ብሒል አትመራምና።
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን እየተለማመደች ነው፤ ልምምዷ ግን እንከን የሌለበት፤ ጎዳናው ያማረ፤ መንገዱ የሰመረ አይደለም። ፈተናዎች ያሉበት ነው እንጂ። የዴሞክራሲን ልምምዷን ለማሳደግ፤ ዴሞክራሲንም በሀገር ላይ ለማንበር ደግሞ ምርጫዎችን በተደጋጋሚ አካሂዳለች። ዴሞክራሲ ያለ ምርጫ አይሳካም፤ ምርጫም ያለ ዴሞክራሲ አይታሰብምና።
ባለፉት ዓመታት ስድስት ጊዜ ምርጫዎችን ያካሄደችው ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ደግሞ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካሂዳለች። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብዙ መልካም ነገሮችን ተመልክታለች። ሚሊዮኖች በሰልፍ ቆመው ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጽናት ድምጻቸውን ሰጥተዋል፤ ሥልጣን በምርጫ እንጂ በኃይል ሊኾን እንደማይችል በድምጻቸው አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ግጭት ሳይኾን ውይይት፤ ጦርነት ሳይኾን ሰላም እንደሚያስፈልግ በካርዳቸው ተናግረዋል።
በብልሃት የሀገራቸውን መንግሥታዊ ሥርዓት ለማጽናት በጽናት ቆመዋል፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ለሰላም እና ለአንድነት ያላቸውን ቀናኢነት በግልጽ አሳይተዋል። ኢትዮጵያም በብልህ ልጆቿ ኮርታለች፤ ደስም ተሰኝታለች። ሀገር ሁልጊዜም በብህል ልጆቿ ትኮራለችና።
ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫ ድረስ ያለው ሂደት ሰላማዊ ነውና ኢትዮጵያ በልጆቿ ብልሃት አሸንፋለች፤ በልጆቿ አስተዋይነት፤ አርቆ አሳቢነት እና ታጋሽነት ድል አግኝታለች። ልጆቿ ባሳዩት ትዕግሥት እና አስታዋይነት ደግሞ ትኮራለች።
ኤፍሬም ማዴቦ ኢትዮጵያ እና ሕገ መንግሥታዊ ምርጫዎቿ በተሰኘው መጽሐፋቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከሌሎች ሥርዓቶች ለየት የሚያደርገው በዓለማችን ካሉት የፖለቲካ ሥርዓቶች ሁሉ የተሻለ ሥርዓት በመኾኑ ብቻ አይደለም ይላል።
ዴሞክራሲ ከሌሎች ሥርዓቶች የሚለየው ሀገራት ፈልገውት እና ሕዝብ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ የሚገነባው ሥርዓት በመኾኑ እንደኾነም ገልጿል።
በዓለም ላይ ዴሞክራሲን ወድዶ እና ፈልጎ እንጂ በግዳጅ የተቀበለ ሕዝብ ወይም ሀገር የለም፤ ከኖረም የግዳጅ ዴሞክራሲ አይሰምርም፤ ዴሞክራሲ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሲታይ ሕዝብ መሪዎቹን መርጦ እራሱን በራሱ የሚያሥተዳድርበት የፖለቲካ ሥርዓት ነውና የዴሞክራሲን ሕዝባዊነት በተመለከተ በሀገራት መካከል ልዩነት የለም ነው የሚሉት።
የምርጫ ሥርዓቱ ውጤታማ ሲኾን ሥልጣን የሚይዘው ፓርቲ እና መንግሥት የተሳለጠ አሠራር እንዲኖራቸው ያደርጋል። መንግሥታዊ መረጋጋትን ይፈጥራል፤ በተለይ አንድ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን በተረጋጋ ሁኔታ ለመጨረስ ዕድል ያገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ውክልና ጠንካራ እና ሕጋዊ ቅቡልነት ይኖረዋል፤ የፖለቲካ ሥርዓቱ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን የማብረድ ችሎታ ይኖረዋል፤ ሕዝብም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ ያለው ተዓማኝነት እያደገ ይሄዳል፤ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ይጨምራል ይላሉ። ይህ ሲኾን ደግሞ ዴሞክራሲ እየጎለበተ ይሄዳል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ አንደበት ካልተለዩ ሃሳቦች መካከል አንዱ “ከአሁን በኋላ በሕዝብ ላልተመረጠ መንግሥት አንገዛም” የሚል በጣም ግዙፍ እና ትርጉም አዘል ሃሳብ ነው የሚሉት ጸሐፊው ይህ ሃሳብ ሕዝብ የመንግሥት ሥልጣን ትክክለኛ ምንጭ እና ባለቤት እንደኾነ እና የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጠው ደግሞ በምርጫ እንደኾነ ያመለክታል ይላሉ።
ኢትዮጵያውያንም ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ከንጋት እስከ ሌሊት ቆመው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። ሥልጣን ከሕዝብ ብቻ እንደሚመነጭ። በዚህ ጠንካራ ሃሳባቸው እና ጽኑ አቋማቸውም ሀገራቸውን አሸናፊ አድርገዋል፤ እነርሱም አሸናፊዎች ኾነዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
