
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በማረስ ከ205 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ሰብል ለማምረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ለአሚኮ ገልጸዋል።
ዕቅዱን ለማሳካት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


ክልሉ በዚህ ዓመት፦

8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት አቅዷል። ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው የክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ዕቅድ ወደብ ላይ ደርሷል።

3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ክልሉ ተጓጉዞ ደርሷል። ከባለፈው ዓመት ተርፎ የነበረ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ክልሉ ውስጥ መኖሩን አንስተዋል።

በጥቅል 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለሥርጭት ቀርቧል። እስከ አሁን ባለው ጊዜም አርሶአደሮች ገዝተው የወሰዱት እና የተሠራጨው 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደኾነ ተናግረዋል።
ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው ነው የገለጹት። ለስርጭት የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ቀድመው ከሚዘሩ ሰብሎች አኳያ በጥሩ የሚታይ እንደኾነም አንስተዋል።

በሌላ በኩል፦

220 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ታቅዷል።
እስከ አሁን ባለው ጊዜ 208 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ድልድል ተደርጓል።

72 ሺህ ኩንታል የሚኾነው የሰብል ምርጥ ዘርም ተሠራጭቷል።