
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን የወረታ ከተማ አሥተዳደር የልማት እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
የወረታ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጌትነት ፈረደ ከተማዋ የብዙ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች መተላለፊያ እንደመኾኗ በየጊዜው የመንገድ ጥገና፣ የውኃ ማፋሰሻ ዲች እና መሰል ልማቶችን በመገንባት ከተማዋን ለነዋሪዎች እና ለተጓዦች ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተማዋን በሚፈለገው ልክ ለማልማት የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አንስተዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ወረታ ከተማ በዞኑ ከፍተኛ የንግድ እና የልማት እንቅስቃሴ ያለበት ከተማ መኾኗን ተናግረዋል።
ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ማኅበረሰባዊ እና አካባቢያዊ አቅሞችን በመጠቀም ከተማውን ለማልማት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ወረታ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴ መተላለፊያ በመኾኗ ማልማት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዋናውን የአስፋልት መንገድ በግራ እና በቀኝ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሣይ ዳምጤ ወረታ ከተማ ለልማት ምቹ መኾኗን ጠቅሰዋል። በቁርጠኝነት ማልማት፣ ማስዋብ እና ጽዱ ማድረግ ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከነዋሪዎች ይጠበቃል ብለዋል።
ለዚህም ማኅበረሰቡ በበጀት መደገፍ እና የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
