
ደብረብርሃን: ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ድህረ ምርጫው ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንዲኾን በሕዝብ ድምጽ ከሚመረጠው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉ የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች ተናገሩ።
ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እየተለጠፈ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ምርጫው ፍፁም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መልኩ መጠናቀቁን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ተወካይ እጩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሠማ ገልጸዋል።
ሕዝቡ በሰጠው ድምጽ ከሚመረጠው ፓርቲ ጋር ለሀገር አንድነት እና ለጋራ ልማት በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ሕዝባችን ወደ ልማት ሥራው እንዲያተኩር እና ወደ ተለመደ ተግባሩ እንዲመለስ እና ድህረ ምርጫው ሰላማዊ እንዲኾን እንሠራለን ያሉት ደግሞ የአርጎባ አንድነት ጁበርቲ ፓርቲ እጩ ሀያት ኡስማን ናቸው።
ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በይፋ የሚገልጸውን ውጤት ጨምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች የተለጠፈውን ውጤት በጸጋ ተቀብለናልም ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ ይርጋለም ምሥጋናው ኅብረተሰቡ አምኖ የኔ ድምጽ ዋጋ አለው በማለት በነቂስ ወጥቶ ስለመረጠ ሊመሠገን ይገባል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ሁሉ ድህረ ምርጫውም ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንዲኾን ፓርቲዎች ሀገራዊ ኅላፊነታቸውን በጋራ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ድኅረ_ምርጫ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ብርቱካን ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
