
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በወርኃ ሚያዝያ እና ግንቦት በርካታ ቁልፍ ተግባራትን ፈጽመዋል።
👉የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ፣ የረጅም ጊዜ የኢንዱስትሪ እድገትን እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ የአምራች ዘርፉ እንቅስቃሴዎችን በንቃት መርተዋል።
በዚህም የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ላይ ያተኮረውን 4ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የከፈቱ ከፍተዋል። የወጣቶችን የሥራ እድል ለማስፋፋትም በአዲስ አበባ የሚገኘውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል። በተጨማሪም የታዳሽ ኃይል አቅምን ለማሳደግ አዲስ ሥራ የጀመረውን የጎበዜ የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካን፣ የአካባቢውን ጥሬ እቃዎች በመጠቀም የገቢ ምርቶችን ለመተካት ያለመውን በሞጆ ከተማ የሚገኘውን የግራንደር የሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካንም መርቀው ከፍተዋል።
👉 የላቀ የጤና ስርዐትና ዘመናዊ አገልግሎቶች
ኢትዮጵያ በልዩና በላቀ የሕክምና ብቃት ቀጣናዊ ማዕከል ለመኾን የምታደርገውን ስትራቴጂካዊ ጉዞ ግብ ለማሳካት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅግ በዘመኑ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች እና በሮቦቲክስ የታገዘውን፣ የካንሰር እና የልብ ሕመሞችን በሀገር ውስጥ ለማከም የተገነባው ዘመናዊውን የላፍቶ ሆስፒታል በአዲስ አበባ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሕክምና ሥልጠና ላይ ለሚገኙ የሩዋንዳ እና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ይፋዊ የእራት ግብዣ አድርገዋል፡፡
👉መሠረተ ልማት፣ ዘላቂ አገልግሎቶች እና ትራንስፖርት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግድና ማኅበራዊ ትስስርን የሚጠናክረውን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የኾነውን አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መርቀዋል።
በጎመሌ ወረዳ የሚገኘውን የደሴ ጎራ ግድብን ጨምሮ የፊና ኦሮሚያ መስኖ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ተከታትለዋል። ንጹህ ውኃ ለማቅረብ እና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የድርቅ መቋቋም አቅምን ለመገንባት የተነደፈውን መጠነ ሰፊ የቦረና የውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፋፊያ ሥራ ጉብኝትንም በበላይነት መርተዋል።
👉 የግብርና ትራንስፎርሜሽን እና የምግብ ሉዓላዊነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የኩታ ገጠም እርሻን ለማስፋፋት በዋና ዋና የግብርና ክልሎች የመስክ ጉብኝት አድርገዋል። በዚህም የሀገር ውስጥ የዩሪያ ማዳበሪያ ምርትን ለማሳደግ የታቀደውን የፋብሪካ ግንባታ ሂደት ለመገምገም ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር ወደ ጎዴ ተጉዘዋል፡፡ በምሥራቅ ቦረና ዞን በሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች እና እማወራዎችን ያሳተፈውን መጠነ ሰፊ የኩታገጠም ግብርና ንቅናቄ ጎብኝተዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን በብዙ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘውን የስንዴ እርሻ ልማትም ጎብኝተዋል፡፡
👉 የሚዲያ እና የብሔራዊ ፖሊሲ ሉዓላዊነት
የመንግሥት ተቋማትን እና የብሔራዊ ፖሊሲ ነጻነትን ለማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ላይ ተገኝተዋል። ዲጂታላይዝድ ወደኾነ እና ራሱን ወደቻለ የስታቲስቲክስ ማዕቀፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ሽግግር ለመደገፍ “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ መልዕክት በተዘጋጀው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል። በተጨማሪም የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ትግበራ ምዕራፍ ሊሸጋገር የቀረበውን ይፋዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ተቀብለዋል።
በዚሁ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብሔራዊ ልማት የሚረዱ የሚዲያ ስነ ምግባር ሙያዊ መመሪያዎችን አስምረው የተናገሩበት እና “የሚዲያ እመርታ ለሀገር ግንባታ” በተሰኘው ብሔራዊ መድረክ ላይ ለሚዲያ ዘርፍ መሪዎች እና ባለሙያዎች ንግግር አድርገዋል።
👉የባሕል ጥበቃ እና አከባቢያዊ እንክብካቤ
በኦሮሚያ ክልል የገዳ ሥርዓት ታሪክን እና ፍልስፍናን ለመጠበቅ በያቤሎ ከተማ የተገነባውን የቦረና ባሕል ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርቀው ከፍተዋል። ማዕከሉ በመደመር መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ የተደገፈ እንደኾነም ይታወሳል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ የዱር እንስሳትና ብዝኃ ሕይወት መጠበቂያ ኾኖ የሚያገለግለውን የቦረና ብሔራዊ ፓርክ መርቀው ከፍተዋል።
👉 ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ማዕቀፎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ አጋርነት ለማጠናከር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያይተዋል። በብድር እና ተለያዩ ዘርፎች አጋርነት ላይ ስምምነቶችን አድርገዋል። በናይሮቢው አፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከተገበረቻቸው የልማት ሞዴሎች ልምድ ከማካፈላቸውም ባለፈ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሪስታሊና ጆርጂየቫ ጋር የኢኮኖሚ ምክክር አድርገዋል። በዚሁ ወር በጅቡቲ የፕሬዝዳንት እስማኤል ዑመርጌሌን በዓለ ሲመት ላይ ታድመዋል። ከኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብ ዬተን ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ የቴምብር ስብስብ ይፋ አድርገዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
