በጎንደር ከተማ የተገነባው የሴቶች እና የሕጻናት የተሃድሶ ማዕከል ተመርቆ ሥራ ጀመረ።

9

 

በጎንደር ከተማ በ115 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው የሴቶች እና የሕጻናት የተሃድሶ ማዕከል ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ ለሚሠራው
ለዩሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት የተሃድሶ ማዕከሉን እንዲያሥተዳድር የሰነድ ርክክብ አድርጓል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የክልሉ መንግሥት የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጥ የተሃድሶ ማዕከላትን እየገነባ መኾኑንም ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ የተገነባው እና ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የኾነው ማዕከል አገልገሎቱን ተደራሽ ለማድረግ መሠራቱን አንስተዋል። ማዕከሉ ለጎንደር ቀጣና አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

በማዕከሉ ውስጥ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕፃናት የጤና፣ የሥነ – ልቦና እና የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በዚህ ማዕከል ለሴቶች ሙያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ጌታሁን ከዚህ ቀደም ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሕክምና ካገኙ በኋላ የሚያርፉበት ማዕከል አለመኖሩ ፈታኝ እንደነበር አስታውሰዋል። የማዕከሉ ወደ ሥራ መግባት ችግሩን በእጅጉ የሚቀንስ መኾኑን ጠቅሰዋል። ጎንደር ከተማ ላይ አገልግሎት እንዲጀምር በመደረጉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ማዕከሉን ሥራ ለማስጀመር የተረከበው እና ወደ ሥራ የገባው ዩሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ከዚህ ቀደም ሢሠራ መቆየቱ ተገልጿል። በቀጣይም መንግሥት እና ሕዝብ የጣለበትን አደራ በኀላፊነት እንደሚወጣ የማዕከሉ ሱፐርቫይዘር እና የዩሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት የጎንደር ፕሮጀክት አስተባባሪ ፅጌ ማርያም ፈንታው ገልጸዋል።

ድርጅቱ ለሴቶች እና ለሕጻናት የተሻለ ሕይወትን መፍጠር ዓላማ አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ሴቶች ፆታዊ እና አካላዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በጋራ መከላከል እና ከጎናቸው መቆም እንደሚገባም አንስተዋል። ይሁን እንጅ ጥቃት ከደረሰ በኋላ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ስለሚያጋጥም ከዚህ ችግር እንዲሻገሩ እና የተሻለ ሕይወትን እንዲመሩ እንደሚሠሩ አብራርተዋል።

ዛሬ የተረከቡት እና ሥራ የጀመሩበት ማዕከልም ተደራሽነታቸውን ከፍ በማድረግ ምቹ እና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ዩሪካ እየሠራ ያለውን አገልግሎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ማዕከሉን በኀላፊነት ስላስረከባቸውም አመሥግነዋል።

#የአሚኮ_ዜና #የሴቶች_ጥቃትን_መከላከል #ጎንደር #አማራ_ክልል

#ጎንደር: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article” በድርጊታችን ተጸጽተናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች