የቻግኒ ከተማን ውበት እየገለጠው ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ

11
እንጅባራ: ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መቀመጫ እንጅባራ ከተማ በ53 ኪሎ ሜትር ርቀት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ መተላለፊያ ኮሪደር ላይ የምትገኘው ቻግኒ ከተማ ኢትዮጵያውያን በፍቅር የሚኖሩባት ውብ ከተማ ናት።
ከተማዋ ባላት ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴም ብዙዎች ሠርተው ለመለወጥ ምርጫቸው ያደርጓታል። በከተማዋ በመገንባት ላይ የሚገኘው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ሌላኛው የውበት ገጿን እየገለጠላት ይገኛል።
በቻግኒ ከተማ ለረጅም ዓመታት እንደኖሩ የሚናገሩት አቶ ጌታሁን ደሴ እና አቶ አያናው አማረ በከተማዋ ለረጅም ዓመታት ሲኖሩ ሃብት አፍርተው ወደ ሌላ አካባቢ የሚሄዱ እንጂ ከተማዋን የሚያለሙ ብዙም እንዳልነበሩ ይናገራሉ። በመንግሥት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ግን ይህንን ቁጭታቸውን የሚሽርላቸው መኾኑን ነው የተናገሩት።
የከተማዋ መልማት የንግድ እንቅስቃሴን ይበልጥ ለማሳለጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ዜጎች ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማስቻል ፋይዳው የጎላ መኾኑንም አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ለፍፃሜ እንዲበቃ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ተናግረዋል።
የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገበየሁ አልማው በመጀመሪያው ዙር የግንባታ ምዕራፍ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የ1ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ከ75 በመቶ በላይ የሚኾነው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ቀሪ ሥራዎችን በዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመደገፍ፣ ግንባታው የሚነካቸውን ቤቶች በማፍረስ እና ለግንባታው ጥራት ገንቢ ሃሳብ በመለገስ ለከተማዋ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል ነው ያሉት።
የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለኑሮ ተስማሚ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመከናወን ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በከፍተኛ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ታጅቦ በመገንባት ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማትም የዕቅዱ አንድ አካል መኾኑን ገልጸዋል። ለማልማትም ኾነ ከልማቱ ተጠቃሚ ለመኾን ሰላም ዋናው ማሣሪያ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ፦ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ሚሊሻው የሕዝባዊነትን ትርጉም በተግባር ያሳየ ኃይል ነው” ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ
Next article“7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና የምርጫ ዕድገት ሂደት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ነው” የኢጋድ ታዛቢዎች ቡድን