
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ግንቦት 29/2018 ዓ.ም በክልል ደረጃ የሚካሄደውን የሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምሥርታ በዓል እና የእውቅና መርሐ ግብር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ የሚሊሻ 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል የሚሊሻውን ታሪካዊ ተጋድሎ እና መስዋዕትነቱን ለመዘከር የታሰበ ነው ብለዋል።
በዓሉ ለሚሊሻ አባላት እና ለቤተሰቦቻቸው ክብር እና ምስጋና ለማቅረብ፤ ተቋማዊ ሪፎርም እና ዝግጁነቱን ለማረጋገጥ፤ የሕዝቡን እና የሚሊሻውን ትስስር ለማጥበቅ እና ሌሎች ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳሉትም አንስተዋል።
ግንቦት 29/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ሚሊሻ የ30 ዓመታት የጀግንነት እና የሕዝባዊነት ጉዞ የሚከበርበት ልዩ ቀን እንደኾነም ገልጸዋል።
የሚሊሻ 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲባል የሚሊሻ ምስረታ ዕድሜው 30 ዓመት ነው ለማለት ሳይኾን በክልል ደረጃ የተቋቋመበትን ለመግለጽ እንደኾነም ተናግረዋል። ሚሊሻ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ ዘመናዊ ወታዳር ባልነበረት ወቅትም ነበር ብለዋል።
ባለፉት ሦሥት አስርት ዓመታት የክልሉ ሚሊሻ በርካታ ታሪካዊ ምዕራፎችን ማለፉንም ገልጸዋል።
ሚሊሻው መደበኛ የሥራ ድርሻውን ሳያስተጓጉል በአንድ እጁ አምራች በሌላ እጁ ደግሞ የሰላም ዘብ በመኾን “የሕዝባዊነትን ትርጉም በተግባር ያሳየ ኃይል ነው” ብለዋል።
ሀገራዊ የሉዓላዊነት ፈተናዎች እና ክልላዊ የጸጥታ ስጋቶች ባጋጠሙ ጊዜያት ሚሊሻው ከመከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰለፍ በደም እና በአጥንቱ ደማቅ ታሪክ መጻፉን ገልጸዋል።
በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ የበኩሉን ሚና ተጫውቷልም ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን 30ኛ ዓመት በዓል ሲያከብር ወደፊት የክልሉን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስከበር እና የሰላም ጥሪ ተግባራት ላይ በትኩረት ለመሥራት ታሳቢ አድርጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
