
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ኅብረት እና ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሂደት በስኬት በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን ብሏል።
ለዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች፣ ለበጎ ፈቃደኞች፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች እና ምርጫው ስኬታማ እንዲኮን ጊዜያቸውን ለሰጡት ሁሉ ያላውን አድናቆት ገልጿል።
የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የታዛቢ ቡድኖች የነበራቸውን አስተዋጽኦ በበጎ እንቀበላለን ነው ያለው።
የአውሮፓ ኅብረትም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መካሄዱን በደስታ እንቀበላለን ብሏል።
ለምርጫ መሳካት አስተዋጽዖ ያበረከቱትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን እና የሲቪል ማኅበራት ተዋናዮችን ጥረት እናደንቃለን ነው ያለው።
የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ( ኢጋድ) እንደ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የተጫወቱትን ወሳኝ ሚና እንገነዘባለን ብሏል። የታዛቢዎችን ሪፖርት በጉጉት እንደሚጠብቅም አስታውቋል።
በግንቦት 24 ቀን ምርጫ ማካሄድ ያልቻሉ ሁሉም የምርጫ ክልሎች ምርጫውን የማካሄድ ዕድል እንደሚያገኙ ያለውን ተስፋም ገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
