
ሁመራ: ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት የልማቶች ሁሉ ቁልፍ መኾኑን በመረዳት የአካባቢው ተወላጆች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾናቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል።
በዚህም ነዋሪነታቸውን በባሕር ማዶ ያደረጉ ዜጎች ተማሪዎችን እና ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።
ከእነዚህ ዜጎች መካከል ወይዘሮ ዓለም አምባቸው ዞኑ ነጻነቱን ከተቀዳጀ በኋላ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለቁሳቁስ እና ለተማሪዎች ማበረታቻ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የትምህርቱን ዘርፍ እየደገፉ መኾናቸውን የወልቃይት ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ገላዬ ገልጸዋል።
ግለሰቧ ለወልቃይት ወረዳ አራት ትምህርት ቤቶች እና ለቃብትያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህረት ቤት በዓመቱ ጋማሽ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 120 ተማሪዎች በድምሩ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የቁሳቁስ እና የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል።
ግለሰቧ በዞኑ እና በወረዳው አጠቃላይ የልማት ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መኾናቸውን የወልቃይት ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ሲሳይ ሙሉ ተናግረዋል። በትምህርት ቤት፣ በመንገድ እና በጤና ጣቢያ ግንባታዎች ላይ የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉም ይገኛሉ ብለዋል።
ትምህርት የልማቶች ሁሉ ቁልፍ መኾኑን በመረዳት የአካባቢው ተወላጆች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ገብረ ማርያም መንግሥቴ ናቸው።
የዞኑ የትምህርት ተቋማት በሀገሪቱ የተከሰተውን የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በርካታ መሠረተ ልማታቸው የወደሙባቸው መኾኑን በመረዳት ግለሰቦች በተማሪዎች እና በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸውን መምሪያ ኀላፊው አድንቀዋል።
የትምህርትን አስፈላጊነት በመረዳት ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ እንዲያስተምሩ ወይዘሮ አለም አስገንዝበዋል። ተማሪዎችም ጠንክረው ተምረው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ መክረዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
