
ደብረብርሃን፡ ግንቦት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ የምርጫ ክልሎች የተካሄደው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊ፣ አካታች እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ መጠናቀቁን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
በመሀል ሜዳ የምርጫ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) በመወከል ለክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ኾነው የቀረቡት ወይዘሮ ቤተልሔም አበራ እንዳሉት የምርጫ ሂደቱ ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ መልኩ አወዳዳሪ እና አካታች ነበር።
ሕዝቡ ለመምረጥ ያሳየው ትጋት እጅግ የሚበረታታ እንደነበር የጠቆሙት ተወዳዳሪዋ ፓርቲያቸው የምርጫውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በአረርቲ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ዕጩ ኾነው የቀረቡት የአርጎባ አንድነት ጄበርቲ ፓርቲ ሊቀመንበር ሐሰን ሙሐመድ በበኩላቸው መራጩ ሕዝብ ያለምንም ጫና ድምጽ መስጠቱን ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው በአሁኑ ወቅት በየጣቢያው እየተለጠፈ ያለውን ውጤት በቅርበት እየተከታተለ መኾኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል፤ ካሸነፉ ለሕዝብ ለመሥራት፣ ከተሸነፉም ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር በመተባበር ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲን በመወከል በሮቢት ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የተወዳደሩት ኤሊያስ አበበ በበኩላቸው ምርጫው ሥልጣን እና ሕዝብን የማሥተዳደር ኀላፊነት የሚገኘው በሰላማዊ መንገድ እና በሕዝብ ፍላጎት ብቻ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ሕዝብ በተግባር ያሳየበት የታሪክ ምዕራፍ መኾኑን ጠቁመዋል።
የብልጽግና ፓርቲም እንደ ሌሎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉ የምርጫ ቦርድን ይፋዊ ውጤት በጸጋ ለመቀበል እየተጠባበቀ መኾኑን ገልጸዋል።
የፓርቲ ተወካዮቹ ለሂደቱ መሳካት ገለልተኛ በመኾን በብርታት ለሠሩ የጸጥታ መዋቅር፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራት እና ለመላው ሕዝብ የላቀ ምሥጋና አቅርበዋል።
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ_ውጤት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
