🚀 ቀጣሪ ድርጅቶችን እና ተመራቂዎችን በማገናኘት የሥራ ዕድል መፍጠር ወሳኝ መፍትሔ ነው። ✨

1

 

#ባሕርዳር፡ ሰኔ 25/2018 ዓ.ም ባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሠለጠኑ እና ብቁ የኾኑ ተመራቂዎቹን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝበትን ሁለተኛ ዙር የሥራ ትስስር አውደርዕይ አካሂዷል።

በአውደርዕዩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ እና የኮሌጁ የቦርዱ ሠብሣቢ ብርሃን ንጉሴ በከተማዋ ሥራ የጀመሩ ከ293 በላይ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በዚህ በጀት ዓመት ብቻ 23 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከጊዜያዊ የሥራ ዕድል በተጨማሪ ለ6 ሺህ 545 ወጣቶች በኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፍ ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ነው የጠቀሱት። ሀገር በኢኮኖሚ እንድትሻገር እና እንድትበለጽግ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የዛሬው የምሩቃን እና ቀጣሪ ድርጅቶች ትስስርም አንዱ ተግባር እንደኽነ ገልጸዋል።

ተቀጣሪ ምሩቃን ሥራን የሚወዱ፣ በባለቤትነት ስሜት እና በታማኝነት የሚያገለግሉ እንዲኾኑ፤ ባለሀብቶች ደግሞ የድርጅታቸውን ኢኮኖሚ የሚያሻሽሉ፣ የሠለጠኑ እና የበቁ ምሩቃንን እንዲቀጥሩ እና ልምድ በማካፈል የራሳቸውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚፈጥሩ ትውልዶችን እንዲያፈሩ አሳስበዋል።

ከአማራ ክልል የሥራ እና ክህሎት ቢሮ የመጡት ሙላው ልመንህ የኮሌጁ ውጤታማነት የሚታየው ተመራቂዎችን እና ቀጣሪ ድርጅቶችን ማገናኘት የሚችል አጋጣሚ ሲፈጠር መኾኑን ተናግረዋል። እንደዚህ ዓይነት ያልተለመዱ እና ከጊዜ ወደጊዜ እያደጉ የመጡ አሠራሮች በቀጣይም ተግባራዊ ለማድረግ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ መር ሥልጠና ሲባል ቀጣሪ ድርጅቶችን እና ተመራቂዎችን በማገናኘት የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት መንገድ ነው ብለዋል።

የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ፈለቀ ውቤ ተቋሙ በዓመት በአማካይ ከ4 ሺህ በላይ መደበኛ እና ከ600 በላይ የቅዳሜ እና እሑድ ሠልጣኞችን እያሠለጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን በዓመቱ ማሠልጠኑን ገልጸዋል።

የዛሬው የትስስር መድረክ🤝 በኢንዱስትሪዎች እና በኮሌጁ መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ ማጠናከር💼 በቀጣሪዎች እና በተመራቂዎች መካከል ቀጥተኛ እና የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር ያለመ መኾኑ ተመላክቷል።

ያሠለጠናቸውን ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማስተሳሰር ሥራን በልዩ ትኩረት እየሠራ የሚገኘው ኮሌጁ ቀደም ሲልም የመጀመሪያውን ዙር የብቁ ተቀጣሪዎች እና የቀጣሪ ድርጅቶች ማገናኛ አውደ ርዕይ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን አስታውሰዋል።

በአውደርዕዩ የመመረቂያ ሥራ ያቀረቡት ተመራቂ አማኑኤል እሸቴ እና ጓደኞቹ የወዳደቁ የፕላስቲክ ምርቶችን ሠብሥበው ከአሸዋ ጋር በመቀላቀል ለተለያዩ ጥቅም የሚውሉ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ማሽን መሥራታቸውን ገልጸዋል። ከማሽን በተጨማሪ ለኮሪደር ልማት እና ለቤት ውስጥ ወለል የሚኾኑ ንጣፎች ማምረታቸውንም አንስተዋል።

ከኮሌጁ ውጭ የሸንኮራ አገዳ ጁስ መፍጫ ማሽን እና አንድ ሰው የሚያንቀሳቅሳት በውኃ ላይ ተንሳፋፊ ብስክሌት መሥራት መቻላቸውን አንስተዋል።

ተመራቂ ማስተዋል ተመቸው እና ጓደኞቿ ደግሞ ኀይል ማመጣጠኛ ሲስተም መሥራታቸውን ተናግረዋል። በፋብሪካዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና አደጋ ሲከሰት የድምጽ አላርም ያለው፣ ምልክት የሚያሳይ እና ለአካባቢው ኦፕሬተሮች በቀጥታ መልዕክት የሚልክ ሲስተም እንደሠሩ ነው የገለጹት።

እነዚህ ሲስተሞች የፋብሪካዎችን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ከማሳድግ ባሻገር በኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ አደጋ እና የኀይል እጥረት ጉዳት የሚደርስባቸውን ማሽኖች በማዳን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን አመላክተዋል።

በአውደ ርዕዩ ከተገኙ ቀጣሪ ድርጅት መካከል የዩኒሰን ዘይት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ታረቀኝ ማኑፋቸሪንግ ዘርፋ የሚመራው በእንዲህ ዓይነት ዘርፎች መኾኑን ተናግረዋል። ተመራቂዎች በቅተው ሲመጡ ዘርፉን እንደሚያግዙ ገልጸዋል።

ኮሌጁ እያሠለጠነ ለድርጅቶች ሲያቀርብ የአቅም መገንቢያ ሥልጠናዎችን ደግሞ ድርጅቶች በማከል ምሩቃን አሁን በተግባር ካሳዩት በተሻለ መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። በየዓመቱ ከዚህ ተቋም ለሚመረቁ ምሩቃን የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ በድርጅታቸው ተግባራዊ ልምምድ እንዲያደርጉ ሲያግዙ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

#BahirDarPolytechnic #JobFair2018 #CareerLink #የሥራዕድል #ባሕርዳር

🎤 ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ ነው።