
ባሕርዳር፡ ግንቦት 25/2018 ዓ.ም(አሚኮ) በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ ስኬት፣ ሥልጡን እና ሕዝባዊ ተሳትፎ በጎላበት መልክ በታላቅ የሕዝብ ድል መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ተወዳዳሪ የሌለው ሚና ለተጫወቱት የክልሉ ፖሊስ፣ ለጀግናዉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል የጸጥታ እና የብሔራዊ ደኅንነት አካላት ፣ለክልሉ ሚሊሻ፣ ሰላም አስከባሪ እና ለመላዉ ሕዝብ ምስጋና አቅርቧል።
ሁልጊዜ ሰላም እና ልማትን ቀዳሚ የሚያደርገው የክልሉ ሕዝብ የምርጫ ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ በምርጫው ዕለት በታላቅ ትዕግስት እና ሥነ ሥርዓት ድምፅ እስከመስጠት ድረስ ያሳየው ፍቅር እና ሀገር ወዳድነት የታሪክ ማህደር የማይረሳው መኾኑን ገልጿል።
በምርጫው ዕለት ኅብረተሰቡ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በመውጣት በክልሉ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ያከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ያለምንም መሰላቸት እስከ ምሽት ሰአት መከናወኑን አረጋግጧል።
ኅብረተሰቡ ረጅም ሰልፎችን በታጋሽነት በመሰለፍ፣ የመምረጥ መብቱን በአግባቡ መጠቀሙ የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ ባሕሉን ያሳየበት እና ለምርጫው ስኬታማነት ትልቁን ድርሻ ያበረከተበት መኾኑንም ጠቁሟል።
ምርጫው የክልሉን ሕዝብ ብስለት፣ ሰላም ወዳድነት እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ለዓለም ያስመሰከረበት ታሪካዊ ምዕራፍ መኾኑንም ዋና ጠቅላይ መምሪያው አመላክቷል።
የጸጥታ ኃይሉ ሂደቱን በበላይነት በመምራት፣ የእያንዳንዱን አካባቢ ኅብረተሰብ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ በማንቀሳቀስ፣ ከሕዝብ የተውጣጡ የሰላም ኮሚቴዎችን እና አደረጃጀቶችን ከራሱ የጸጥታ መዋቅር ጋር በማስተሳሰር የጋራ የሰላም ግንባር መፍጠር በመቻሉ ሰላሙን ማረጋገጥ መቻሉንም አስታውቋል።
ይህንን ሥራ ስኬታማ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሉ አባላት ሌት ከቀን ያሳዩት ከፍተኛ ልፋት፣ ድካም እና ተጋድሎ በአንዳንድ ቦታዎች የምርጫውን ሂደት ለማደፍረስ እና ሁከት ለመፍጠር አልመው የተንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ አካላትን የጥፋት ሴራ ቀድሞ በተዘጋጀ ስልታዊ የመከላከል እቅድ ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉንም አመላክቷል።
የጸጥታ ኃይሉ የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ የመወጣት ጀግንነት፣ ሙያዊ ብቃት እና የገባውን ቃልኪዳን በታማኝነት በመፈጸም የሕዝቡን ደኅንነት በልዩ ጥንቃቄ የማስጠበቅ ሥራ፤ ከተቋማዊ ኩራት ባሻገር ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ታላቅ ክብርን ያጎናጸፈ ተግባር በመኾኑ ላቅ ያለ ምስጋናና እውቅና ሰጥቷል ነው ያለው።
ምርጫውን ለማወክ የሞከሩ ማናቸውንም የጸረ ሰላም ኃይሎች የጥፋት አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ያከሸፈ ታላቅ የሕዝብ ድል የተመዘገበው ሕዝቡ ያሳየው አስተዋይነት እና የሰላም ባለቤትነት ስሜት በመኖሩ እንደኾነም አንስቷል።
ለታሪካዊ ድሉ መገኘት ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም፣ መረጃዎችን በወቅቱ በመለዋወጥ እና ለሰላም ጥበቃው ግንባር ቀደም ጠባቂ በመኾን ያሳየው ጠንካራና የተቀናጀ ጥምረት ዋነኛ መሠረት ነበር ተብሏል።
በምርጫው ወቅት የታየውን መልካም የሕዝብ፣ የፖሊስ ቅንጅታዊ አሠራር እና አደረጃጀት ይበልጥ በማጠናከር የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በቀጣይም በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራት፣ ለመገናኛ
ብዙኃን ተቋማት፣ ለውጭ እና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች እና ለሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ በሙሉ ምስጋና አቅርቧል።
ከአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ በጋራ ለማስቀጠል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
