
ኢትዮጵያ ከዜጎቿ የፈለገችዉን ኹሉ በፈለገችው ጊዜና ኹኔታ የምታገኝ ሀገር ናት፡፡ ለሀገራቸዉ የተጠየቁትን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ ዜጎች ስላሏት በእጅጉ ኮርታለች፡፡ ከዓድዋ እስከ ሕዳሴ ግድብ፣ ከወገን ለወገን መረዳዳት እስከ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎቿን ተሳትፎ ጠይቃ፣ ከመሻቷ በላይ ተሳትክቶላታል፡፡ ዛሬ የተደገመዉም ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን ማንበር፣ በግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥትን መምረጥ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ፅኑ መሠረት ማስያዝ ትሻለች፡፡ ለዚህ ደግሞ 7ኛዉን ጠቅላላ ምርጫ እንደ ትልቅ አጋጣሚ መጠቀም አስፈልጓት ነበር፡፡
በምላሹም ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት ተመዝግበው የምርጫዋን እለት ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ እነሆ የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበል ዜጎች በነቂስ ወጥተው ሲመርጡ ውለዋል፤ ሌሊቱንም አጋምሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ዜጎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፈዉ ድምፅ የሰጡበት ልዩ ምርጫም ነው፡፡
ምርጫዉ እንዳይካሄድ ባዳ እና ባንዳ ተቀናጅተዉ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልደረደሩት እንቅፋት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጠራችው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማይቻል ነገር አልነበረምና በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ኢትዮጵያውን በሰላማዊ መንገድ መርጠው ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጥሪ ተቀብሎ ከንጋት እስከ ምሽት በመምረጥ ምላሽ ለሰጠው ሕዝብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ እንዲጸና እና ዜጎች በሰላም እንዲመርጡ ምቹ ዓውድ ለፈጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየደቂቃዉ ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሁም የምርጫዉን ሂደት ለመሩ፣ ላስተባበሩ እና ለታዘቡ ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 25 2018፣አዲስአበባ፣ኢትዮጵያ
