“ምርጫው ከፍተኛ የሕዝብ ቁርጠኝነት የታየበት ነው”

6

 

ጎንደር: ግንቦት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ እና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በተከናወነው የምርጫ ሂደት ዙሪያ ሀሳብ ሰጥተዋል።

በጋራ ምክር ቤቱ አባል እና የኢሕአፓ ተወካይ ካሳ በለጠ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ ያለምንም ችግር መካሄዱን ተመልክተናል ብለዋል።

ምርጫው የሕዝብ ቁርጠኝነት የታየበት፤ ሕዝቡ የሚፈልገውን በመምረጥ የነቃ ተሳትፎ ያሳየበት እንደኾነም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ወደፊት መጓዝ የሚገባትን የዴሞክራሲያዊ መንገድ እና የሰላማዊ አካሄድን በሚገባ ያስገነዘበ እንደኾነም ተገንዝበናል ነው ያሉት።

ሌላኛው የጋራ ምክር ቤቱ አባል እና የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ መኮነን ብርሃን ሕዝቡ የሚፈልገውን አካል ለመምረጥ ያሳየው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም በሰላማዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠ ሀገራዊ መንግሥት ለመመስረት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየበት ነው ብለዋል። ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መኾኑንም ተመልክተናል ነው ያሉት።

የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የሕዝቡን ድምጽ በማክበር በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን የምክር ቤቱ አባላት አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ምርጫው የዴሞክራሲ ልምምድን ያየንበት ነው” የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን