🇪🇹🗳️ “ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን” አብን

9

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከፍተኛ መሪዎች እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች በባሕር ዳር የምርጫ ክልል በመገኘት ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ እና የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እመቤት ከበደ የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት ዓመታት በተለየ መልኩ የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ እና ዕውነተኛ ፍላጎት የታየበት ልዩ ክስተት መኾኑን ገልጸዋል።

“በአማራ ክልልም ኾነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ሕዝቡ በነጻነት እና በሰላም ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ የተሄደበት ርቀት የሚያበረታታ ነውም ብለዋል። ይህም ሀገሪቱ ለምታደርገው የዴሞክራሲ ልምምድ ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።

የአብን ምክትል ሊቀመንበር እና የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመወዳደር የሕዝብ አማራጭ ኾኖ መቅረቡን አስታውሰዋል።

የምርጫውን ሂደት ከመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ድምጽ እስከመስጠት ድረስ ያለውን ሂደት በቅርበት ሲታዘቡ እንደነበር የገለጹት አቶ መልካሙ ሂደቱ እጅግ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር አረጋግጠዋል።

በየምርጫ ጣቢያው የተሰማሩት የፓርቲው ታዛቢዎች እና ተወካዮች ሂደቱን በአንክሮ መከታተላቸውንም ጠቁመዋል

ማሸነፍም ኾነ መሸነፍ የሚወሰነው በዜጎች ነጻ ድምጽ ብቻ ነው ያሉት ዕጩዎቹ ፓርቲያቸው ሕዝብ የሚሰጠውን ማንኛውንም የድምጽ ውጤት በታላቅ ጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነው ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ_2018 ዓ.ም #ባሕር_ዳር #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያውያን መብታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ ነው” የአፍሪካ ኅብረት የታዛቢዎች ቡድን
Next article🗳️ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እየተከናወነ ነው” የደብረ ብርሃን ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት