
ደብረብርሃን፡ግንቦት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ታሪካዊ ቀን ልዩ ታሪክ ካላቸው መራጮች መካከል የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ የሸዋጣይ ነጋሽ አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ የሸዋጣይ በሀገሪቱ ድምጽ መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአንድም ምርጫ ቀርተው አያውቁም።
ዛሬም ማለዳ ተነስተው ወደ ምርጫ ጣቢያ ያቀኑት እኚህ አንጋፋ መራጭ “ይበጀኛል፣ ይጠቅመኛል” ላሉት እና ላመኑበት ድምጻቸውን በነፃነት ሰጥተዋል።
”ድምፄ ዋጋ አለው፤ የሀገርን እጣ ፈንታ ይወስናል። ለዛ ነው በየጊዜው ላመንኩበት ፓርቲ ድምፄን የምሰጠው” ይላሉ ወይዘሮ የሸዋጣይ።
ምርጫ የነገን እጣ ፈንታ በራስ እጅ የመወሰን መብት እና ኀላፊነት መኾኑን በተግባር ያሳዩት ወይዘሮ የሸዋጣይ ኅብረተሰቡ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በደብረብርሃን ምርጫ ክልል ውስጥ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው በንቃት እየተሳተፉ መኾኑን አሚኮ በምልከታው አረጋግጧል።
ዘጋቢ፦ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
