🇪🇹 ከታሪክ አሻራ ወደ ዴሞክራሲ ፋና

11

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክ፣ የጋራ እሴት እና የማንነት ማኅደር የኾነች የልዩ ልዩ ውብ ሕዝቦች ታላቅ ሀገር ናት። የሰው ልጅ ጥንታዊ ታሪክ ሲመረመር ቀዳሚ ኾኖ የሚገኘው የሉሲ (ድንቅነሽ) እና የሌሎች ቅሪተ-አካላት መገኛነቷ፣ ምድሪቱ የሰው ዘር በሙሉ መገኛ እና የጋራ መነሻ መኾንዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰከረ ሐቅ ነው። ይህ የሰው ዘር መገኛ የመኾን ክብር፣ የሀገሪቱን ጥንታዊነት እና ገናናነት ከፍታ ያሳያል።

ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ውስጥ ሳይወድቁ በነፃነት የኖሩ ኩሩ ሕዝቦች ሀገር ናት። ሀገር ወዳድ እና ኩሩ ሕዝቦቹ በአንድነት በመቆም ዘመናዊ ጦርን በማሸነፍ የዓድዋን ድል አስመዝግበዋል፤ ነጭ በጥቁር ላይ የነበረውን የበላይነት በመሻርም የሰው ልጅን እኩልነት ለዓለም አሳይተዋል።

​ይህ ዓይነቱ የአይበገሬነት ማንነት ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል በመኾን የአፍሪካዊነት ንቅናቄ እንዲቀጣጠል እና እንዲመሠረት ትልቅ መሠረት ጥሏል። ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት እና አንድነት ላበረከተችው የማይተካ ሚና ማረጋገጫ ይኾን ዘንድም የአፍሪካ ኅብረት (ቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ላይ በክብር ከፍ ብሎ እንዲቆም አድርጓል። ይህም የኢትዮጵያ የከፍታዋ አንዱ ምልክት ነው። ታላቋ ሀገር የአፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ መዲና ስለመኾኗም ያረጋግጣል።

​ይህቺ የታሪክ እና የነፃነት ተምሳሌት የኾነች ሀገር፣ ዛሬም ታሪካዊ ገናናነቷን በልማት ለመድገም በትልልቅ አሕጉራዊ እና ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ እየተረማመደች ትገኛለች። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በየዘርፉ የሚገነቡት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቦቿን የጋራ ራዕይ እና የነገ ብሩህ ተስፋ የሚያንጸባርቁ ማሳያዎች ናቸው።

​በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር እና የሕዝብን ሉዓላዊ ሥልጣን በድምጽ የመጠቀም መብትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ የታላቅነት መገለጫ ነው። የአሁኑ ጠቅላላ ምርጫም ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት እና ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የወደፊት እጣ ፈንታ ያላቸውን ከፍተኛ ተሳትፎ እያሳዩበት የሚገኝም መኾን ችሏል።

ምርጫው በታሪካዊ የነፃነት አሻራ ላይ የዴሞክራሲን ፋና በመለኮስ፣ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ለማፋጠን እና የዜጎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍም ነው።

​በምርጫው የሚሰጠው የሕዝብ ድምጽም የልማት ቀጣይነትን፣ የሀገራዊ አንድነትን እና የጋራ ታላቅ ሀገር የመፍጠር ራዕይን ለማሳካትም ወሳኝነት አለው። ይህ የዴሞክራሲ በዓል፣ የሕዝብን የሀሳብ ልዕልና የሚያረጋግጥም ታላቅ ሂደት ነው።

​በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በትላንትና ታሪኳ የሰው ዘር መገኛ፣ በዛሬዋ አፍሪካ የነፃነት እና የአንድነት ማዕከል፣ በነገው ጉዞዋ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና በትልልቅ ፕሮጀክቶች የምትተጋ የታላቅ ሕዝቦች ገናና ሀገር ናት።

#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ_2018_ዓ.ም #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምርጫው የሀገሪቱ የወደፊት መጻኢ ዕድል የሚወሰንበት ነው።