
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ወቅታዊ ጉዳዮችን እና የክልሉን ሰላም አስመልክተው ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ሕዝቡ በነጻነት ድምጹን መስጠት እንዲችል የክልሉ ጸጥታ ኃይል እና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።
የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የሕዝቡን ሰላም ለማስከበር የጸጥታ ኃይሉ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መኾኑን ኀላፊው አንስተዋል።
የምርጫ ቁሳቁስ በሁሉም አካባቢዎች በሚፈለገው ሁኔታ እንዲደርስ መደረጉንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ሥጋት ነጻ ኾኖ ድምጹን እንዲሰጥ የጸጥታ ኀይሉ አስተማማኝ ሁኔታን የመፍጠር ኀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
ምርጫው ስኬታማ ይኾን ዘንድ በምርጫው ዕለትም ኾነ ከምርጫ በኋላ የጸጥታ ኃይሉ ኀላፊነቱን ይወጣል ነው ያሉት።
የጸጥታ ኃይሉ ተልዕኮ ምርጫን በስኬት ማጠናቀቅ ብቻ ሳይኾን በቀጣይም የክልሉን ሕዝብ ሰላም ማረጋገጥ ላይም አጠናክሮ መቀጠል እንደኾነ ነው የገለጹት።
በቀጣይም “ጽንፈኛ ኃይሉ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተጠናከረ ኦፕሬሽን የማድረግ፤ ጽንፈኛ ኃይሉን የማጽዳት እና መሰል ሕግ የማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የጠላት የሰው ኃይል እና የፕሮፖጋንዳ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል ነው ያሉት ዶክተር እሸቱ። ይህ ሊኾን የቻለው የጸጥታ ኃይሉ ከሚያደርገው ሕግ የማስከበር ተልዕኮ ባሻገር ኅብረተሰቡ የታጣቂዎችን የጥፋት ድርጊት ተረድቶ ከመንግሥት ጎን በመቆሙ ነው ብለዋል።
መንግሥት አሁንም ቢኾን የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለሚመጡ ኃይሎች በሩ ክፍት መኾኑንም ገልጸዋል። ይህንን ዕድል በማይቀበሉ አካላት ላይ ግን ሕጋዊ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር እንደሞቀጥል አስገንዝበዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
#አሚኮ_ዜና #ምርጫ_2018
#ሰላም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰአሚኮ_ዜናብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
