
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ 2018/19 ዓ.ም የምርት ዘመን ሰሊጥን ጨምሮ በአኩሪ አተር እና በማሾ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የግብርና መምሪያው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑር ሁሴን አብዱልቃድር አካባቢው በገበያ ተኮር ሰብሎች የሚታወቅ በመኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ በዚህ ዓመት 558 ሺህ 63 ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ እየተሠራ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚኾነው በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተር እና በማሾ እንደሚሸፈን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የአንደኛ እርሻ እና ማሳን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነም ቡድን መሪው አንስተዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም 85 በመቶ የሚኾነውን የማሳ ዝግጅት መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት።
ዞኑ በምርት ዘመኑ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
“ክልሉ የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ማቅረቡንም” አንስተዋል።
በዞኑ የምርጥ ዘር ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እና ምርትን ለማሳደግ ቀደም ሲል በሁመራ የግብርና ምርምር ከወጡት በተጨማሪ የአካባቢ ዘሮችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ግብርና #ወልቃይት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰአሚኮ_ዜናብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
