“የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለምርጫው ያደረገው ዝግጅት ጠንካራ ነው ” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

8

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እና በቴክኖሎጂ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በዋና መሥሪያ ቤቱ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ለጋራ ግብረ ኃይሉ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለምርጫው ያደረገው ዝግጅት እጅግ ጠንካራ ነው ብለዋል።

ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢኾንም መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የጸጥታ እና የደኅንነት ኃይሎች ጋር በመኾን የጥፋት ዕቅዶች ማክሸፉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሪፎርሙ በኋላ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በቴክኖሎጂ መደራጀቱ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ እና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የምርጫ ቁሳቁስ ሥርጭት ደኅንነት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ቀሪውን የምርጫ ሂደት ሰላማዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የኾኑ ሎጀስቲክስ እና ትጥቆች መሟላታቸውን ገልጸዋል። ለተልዕኮው የሚመጥን በቂ ሥልጠና እና መመሪያ የወሰደ የሰው ኃይል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሰማራቱን አስታውቀዋል።

ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጸጥታ እና ደኅንነት የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው
ከምርጫው በኋላ የሚከናወኑ ሂደቶችም በስኬት እንዲጠናቀቁ ግብረ ኃይሉ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበወሰዱት ካርድ የሚኾናቸውን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የጃዊ ወረዳ እና የፈንድቃ ከተማ መንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን አንጎት ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።