
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቂ የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የምርጫ ቁሳቁስ በክልሉ በሚገኝ የምርጫ ክልሎች ያለምንም ጸጥታ ስጋት እንዲደርስ መደረጉንም አስታውቀዋል። መራጩ ሕዝብም በምርጫው ዕለት ያለ ምንም ስጋት ድምፁን መስጠት እንዲችል በየጣቢያዎቹ በቂ የጸጥታ ስምሪት ተደርጓል ነው ያሉት።
የጸጥታ ኀይሉ ሰላምን የማስከበር እና ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ከጸጥታ መዋቅሩ በተጨማሪ መላው ማኅበረሰብ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በንቃት እየተሳተፈ መኾኑን አብራርተዋል። በተለይም ወጣቶች አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ለጸጥታ አካላት በመጠቆም ትልቅ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
“መንገድ ተዘግቷል” በሚል የሚራገበው ፕሮፖጋንዳ የጽንፈኛ ኃይሉ የተለመደ የሐሰት ወሬ ነው፤ በዚህ ወቅት መደበኛ ሥራዎችም ኾኑ ወቅታዊ ተግባራት በአግባቡ እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅትም በክልሉ የምርጫ ቁሳቁስ እና የአፈር ማዳበሪያ በተፈለገው አካባቢ ያለምንም ችግር እንዲደርስ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡም ለተለመደ የመንገድ ተዘግቷል የጽንፈኛ ኀይል የማደናገሪያ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ጀሮ ሳይሰጥ የእለት ከእለት ተግባሩን ያለምንም ስጋት እንዲከውን አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
