የባሕል ፍርድ ቤቶች ግጭትን በዕርቅ የሚያጸኑ፣ ቁርሾ እና ቂምን የሚሽሩ ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

7

 

ደብረብርሃን፡ ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዕውቅና ያገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

በክልሉ ሕጋዊ ዕውቅና የተሰጣቸውን 15 ያህል አለመግባባት መፍቻ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ወደ ተግባር የማስገባት ሥራ ቀደም ብሎ መጀመሩ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንደተናገሩት በክልሉ በሚገኙ 1ሺህ 170 ቀበሌዎች ውስጥ ከአምስት ሺህ በላይ የባሕል ዳኞች ተመርጠዋል።

ከተመረጡት የባሕል ዳኞች መካከል ከ400 በላይ የሚኾኑት ሴቶች መኾናቸውን ገልጸዋል። አደረጃጀቱን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

የባሕል ፍርድ ቤቶች ጊዜን እና ገንዘብን የሚቆጥቡ፣ አሸናፊ እና ተሸናፊ ሳይኖር በዕርቅ የሚያጸኑ፣ ቁርሾ እና ቂምን የሚሽሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ.ር) በሀገሪቱ የሚከሰቱ አለመግባባቶች 43 በመቶ ያህሉ በአማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች የሚፈቱ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ የሕግ ሙግቶቹን በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች አማካኝነት መፍታት የሚመርጥ በመኾኑ በአሁኑ ወቅት በክልሎች ይህንን አማራጭ ሥርዓት ማስጀመር መቻሉን ጠቅሰዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ
የባሕላዊ ግጭት አፈታት ስልት ከማኅበረሰባችን የዘመናት አኗኗር ጋር የተጋመደ፣ ትውልዱም የታላላቆችን ምክር እና ሐሳብ እንዲያከብር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

አሠራሩ በአዋጅ መደገፉ ሕግ እና ባሕልን አጣጥሞ ለመጓዝ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል። ወደ ተግባር ለመግባት እና የፍትሕ ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋት ከፍተኛ እገዛ እንደሚደረግ አንስተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የከተማዋን ፈጣን ዕድገት ተከትሎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች ወሳኝ መኾናቸውን አንስተዋል። ይህንን አሠራር ከከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር አስተሳስሮ ለመተግበር በትኩረት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የባሕል_ፍርድ_ቤት #ደብረ_ብርሃን #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መብታችን ተጠቅመን ድምጻችን ለመስጠት ተዘጋጅተናል” የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች
Next articleለስኬታማ የምርጫ ሂደት የማኅበረሰቡ ሚና ጉልህ ነው።