🗳️ ነጋችሁን በካርዳችሁ ምረጡ !

18

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሕይወት ውስጥ ምርጫዎች አሉ። የወደደውን የመረጠ በወደደው ይኖራል። ያልመረጠ ግን በተመረጠለት የሚኖር ይኾናል።

ኢትዮጵያውያን ነጋቸውን በካርዳቸው እንዲመርጡ አማራጭ ቀርቦላቸዋል። አማራጩ ነገን የመምረጥ፣ ሀገርን ላመኑበት የመስጠት ጉዳይ ነው። ካርዱን በአግባቡ የተጠቀመ በሀገሩ እና በራሱ ነገ ላይ ይወስናል። ካርዱን በአግባቡ ያልተጠቀመ ግን የሀገሩን እና የራሱን ነገ ለሌሎች አሳልፎ ይሰጣል።

በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ዜጎች መንግሥታቸውን በካርዳቸው ይመርጣሉ፤ ሥልጣንንም በካርዳቸው አደራ ይሰጣሉ። ያለ ዜጎች ፈቃድ የሚገኝ ሥልጣን ሕጋዊ አይደለም፤ ቅቡልነትም የለውም። በተለይ በዚህ ዘመን ያለ ካርድ የሚገኝ ሥልጣን ከዘመኑ እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም።

ኤፍሬም ማዴቦ “ኢትዮጵያና ሕግ መንግሥታዊ ምርጫዎቿ በተሰኘው መጻሕፋቸው እስከ ዛሬ ለብዙ ዘመናት ያለ ዴሞክራሲ ተጉዘን ሊኾን ይችላል። ከዛሬ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ያለ ዴሞክራሲ የምታደርገው እያንዳንዱ እርምጃ አንድነቷን ያላላዋል” ሲሉ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ በደረሰበት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ደረጃው ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውጭ መተዳደር አይፈልግም።

ይህ ብቻ ሳይኾን ብዙ ብሔረሰቦች፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች እና የባሕል ስብስቦች የሚገኙባትን ትልቅ ሀገር ከአሁን በኋላ ከዴሞክራሲ ውጭ ማሥተዳደር እንደማይቻል ያለፉት ዓመታት ታሪካችን በግልጽ አሳይቶናል ነው የሚሉት።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ያስፈልጋል ማለት ነው።

ምርጫ ለሁሉም ዜጎች ዕኩል የተሰጠ መብት ነው። የአንድ ሀገር ዜጎች ይሕንን መብታቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙ የምርጫው ሂደት ሁሉም የኅብረተሰብ አባል በቀላሉ የሚረዳው፣ ሳይቸገር እና ሳይጨነቅ ደስ ብሎት የሚሳተፍበት ግልጽ ሂደት መኾን አለበት ነው የሚሉት።

ዜጎችም መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው። ሀገራቸውን የሚወዱ ሁሉ በነገዋ የሀገራቸው እጣ ፈንታ ላይ መወሰን አለባቸው።

ምርጫ የድምጽ ሰጪውን ኅብረተሰብ ጥቅም እና ፍላጎት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲወክል ያደርጋል፤ ጠንካራ እና የተረጋጋ መንግሥት እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ሕዝብ ብቃት ባላቸው አካላት እንዲወከል ያደርጋል፤ የፖለቲካ ባለድርሻዎችን እና ተከታዮቻቸውን ያቀራርባል ይላሉ።

ምርጫ በአንድ በኩል ብቸኛ የሕዝብ ሥልጣን መገለጫ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ ለመኖሩ እና ላለመኖሩ ማረጋገጫ መለኪያ ነው። ዴሞክራሲ እና ምርጫ ተለያይተው መኖር አይችሉምና።

ዴሞክራሲ ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ሁሉ ምርጫ አለ። ምርጫ ባለበት ቦታ ሁሉ የምርጫ ሂደት አለ። ምርጫ በየትኛውም የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ አስፈላጊ ነው። ዴሞክራሲ ደግሞ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎን የሚጠይቅ ሂደት ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከቀናት በኋላ በታሪኳ ለሰባተኛ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ታካሂደላች። ዜጎች በካርዳቸው ለቀጣይ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ለሚመራት አካል ሥልጣን ይሰጣሉ። በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ሥልጣን የሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ይሰጣል፤ ሕዝብም ይነሳል።

ኢትዮጵያውያንም በካርዳቸው ነጋቸውን ይመርጣሉ። የያዙት ካርድ ዝም ብሎ አይደለም፤ ነገን የሚመርጡበት፤ የሥልጣን ባለቤታቸውን የሚያረጋግጡበት፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚወስኑበት፤ በእነርሱ ቦታ እንደ እነርሱ ኾነው የሚሠሩላቸውን ወኪሎቻቸውን የሚመርጡበት፤ ሀገራቸውን እንደሚወዱ የሚያረጋግጡበት፤ የዴሞክራሲያዊ ሥራዓትን የሚያሰፉበት ነው።

በካርዳችሁ ነጋችሁን ምረጡ፤ የሥልጣን ባለቤትነታችሁንም አረጋግጡ።

#አሚኮ-ዜና #ምርጫ2018 #አማራ #ኢትዮጵያ🇪🇹

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🗳️ 🇪🇹በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለምርጫው አስተማማኝ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል።
Next article🗳️ 🇪🇹የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናገሩ።