
አዲስ አበባ: ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ቀን መታሰቢያ ጉባኤ በአፍሪካ የልህቀት አካዳሚ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው “የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ግቦችን ከግብ ለማድረስ ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና አስተማማኝ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ዳይሬክተር መሠረት ደስታ መሪ መልዕክቱ ስለ ሰብዓዊ ክብር፣ ስለ ሰው ልጆች ልማት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለ አመራር ክህሎት የሚናገር መኾኑንም አብራርተዋል።
የውኃ አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ጉዳይ ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ ጉዳዩ የተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ፣ ከጊዜያዊ ጥቅሞች ይልቅ ለረጅም ጊዜ ዘላቂ ተፅዕኖ ቅድሚያ የሚሰጡ መሪዎችን የሚሻ እና ሰዎችን በታማኝነት እና በፍትሐዊነት የሚያገለግሉ ሥርዓቶች መዘርጋትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ከፖሊሲዎች እና ስምምነቶች ባሻገር አፍሪካ ምን ማሳካት እንደምትችል የሚያሳዩ ታላላቅ ተምሳሌቶች አሏት ያሉት ወይዘሮ መሠረት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብንም በምሳሌነት አንስተዋል።
የሕዳሴው ግድብ የአንድ ግድብ ግንባታ ብቻ ሳይኾን የትልቅ ምኞት፣ የጽናት እና የጋራ ዕድገት ማረጋገጫ መኾኑንም አንስተዋል።
የሚመነጨው ኀይል ከድንበር ባለፈ የሌሎችን ሀገራት ኢንዱስትሪዎች የማንቀሳቀስ፣ ቀጣናዊ ትሥሥርን የመደገፍ፣ እንዲሁም ንግድ እና ልማትን የማሳለጥ ከፍተኛ አቅም ያለው በመኾኑ ግድቡ አብሮነትን እና አንድነትን ይወክላል ብለዋል።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ የጋራ የውኃ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ጠንካራ የውኃ ዲፕሎማሲን፣ የተቋማት ዕምነትን፣ ፍትሐዊ ትብብርን እና የቀጣናውን መረጋጋት የሚደግፍ የረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ መዘርጋትን ይጠይቃል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርሆዎች ያላትን ቁርጠኝነት የምታረጋግጥ ናት ብለዋል።
ጉባኤው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ እና የኢትዮጵያ ውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት ሲኾን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈውበታል።
#አሚኮ_ዜና #የአፍሪካ_ቀን #መታሰቢያ_ጉባኤ #አዲስ_አበባ #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
