🌿 በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።

13

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ ስኬታማ ተግባር ለመፈጸም ሰፊ ዝግጅት መከናወኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኅላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ለመጭው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል።

​🌿 1 ነጥብ 78 ቢሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ወቅት ድረስ 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ወይም 97 ነጥብ 3 በመቶ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

🌴 ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ ተለይቷልም ብለዋል።
​የችግኝ መትከያ ጉድጓድ በማዘጋጀት በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሚገኝም ኀላፊው አንስተዋል።
​
በኅብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ የሥራ ባሕል መሻሻልን ያመጣ ሲኾን ማኅበረሰቡ የሥራው ዋና ባለቤት በመኾን ችግኞችን እየተንከባከበ እና ውጤታማ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

​ሕዝቡ ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን እና ጊዜውን በመስጠት ባደረገው ጥበቃ እና እንክብካቤ ከአሁን በፊት የተተከሉ ችግኞች የመፅደቅ መጠን ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።
​
​ይህ ንቅናቄ የአካባቢን ሥነ ምህዳር በመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

“ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች የነገው ትውልድ እስትንፋስ ናቸው” ነው ያሉት። ለምለም እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማሸጋገር ዋስትና እንደኾነም አንስተዋል።

​ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያስተሳሰረ በመኾኑ ይህ የልማት ሥራ የትውልድ ሁሉ ኀላፊነት ተደርጎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
​
ለዚህ ተግባር ስኬትም በየደረጃው ያሉ የዝግጅት ተግባራትን ከወዲሁ በጥራት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚባ አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleሕዝቡ የምርጫው ባለቤት እንደመኾኑ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅም በቅንጅት እየሠራ ነው።
Next article“ሕዳሴ ግድብ የጽናት እና የጋራ ዕድገት ማረጋገጫ ነው” የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ