
ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫው ሊጠናቀቅ 4 ቀን ሲቀረው ያለው ጊዜ “የጥሞና ወቅት” በመባል ይታወቃል።
አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ጉዳዮች የወንጀል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
የጥሞና ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረኩን ለባለቤቱ (ለሕዝቡ) የሚያስረክቡበት ወሳኝ ድልድይ ነው ብለዋል። ይህ ወቅት መራጩ ሕዝብ ያደመጣቸውን የፖሊሲ አማራጮች ሁሉ አመዛዝኖ የልቡን የሚወስንበት የጸጥታ ጊዜ ነው ይላሉ።
በዚህ ወቅት የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ እጩዎች እና ደጋፊዎቻቸው በስብሰባ አዳራሽም ኾነ በመንገድ ወጥተው ምረጡኝ የማለት መብት የላቸውም ነው ያሉት።
ክልከላው በአካል የሚደረግን እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፤ በሬዲዮ፣ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥን እንዲሁም በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ጭምር የምረጡኝ ዘመቻ ማድረግ በሕግ የተከለከለ ስለመኾኑም ባለሙያው ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃን በዚህ ወቅት የምርጫ ቃለ መጠይቆችን ወይም እጩዎችን የሚያወድሱ ዜናዎችን ማሠራጨት አይችሉም ብለዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ብቸኛ ሥራ የምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸውን መመሪያዎች እና መረጃዎች በዘገባ ማስተጋባት ብቻ ይኾናል።
መገናኛ ብዙኃን ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እየተፈጸመ መኾኑን የማረጋገጥ እና ዜጎች ያለምንም ተጽዕኖ በነጻነት የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማገዝ ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የሕግ ጥሰቶች ሲታዩ የማጋለጥ እና ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በተሳሳቱ እና በተጋነኑ የሐሰት መረጃዎች እንዳይደናገር ጋዜጠኞች እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ብቻ ለኅብረተሰቡ የማድረስ ታሪካዊ አደራ አለባቸው ብለዋል።
በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሕግ የሚጥሱ ወገኖች በምርጫ አዋጁ እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት የሕግ ተጠያቂ እንደሚኾኑም አንስተዋል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
