
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል በደሴ ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በዕለቱ የከተማዋና የአካባቢው የእስልምና እምነት ተከታዮች ሶላት በመስገድ በዓሉን አክብረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ፤ የኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል የጽኑ እምነት፣ የከፍተኛ መስዋዕትነትና የፈጣሪ ምህረት መገለጫ ታላቅ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ ሰው ለታላቅ ዓላማ ዋጋ መክፈል እንዳለበትና መታመን ከመስዋዕትነት እንደማይተናነስ የሚያስተምር መሆኑንም አክለዋል።
ይህ ታላቅ በዓል ሀብታም፣ ድሃ፣ ቀለምና ዘር ሳይለይ ሁሉም ሙስሊም በአንድነት ቆሞ የፈጣሪን ታላቅነት የሚገልጽበትና ምህረትን የሚለምንበት ልዩ ዕለት መሆኑን ከንቲባው ጠቁመዋል።
በአኹኑ ወቅት ደሴ ሰላሟን አስጠብቃ የልማት ፍሬዎችን እያጣጣመች ትገኛለች፣ የተጀመረው ረጅሙ የልማት ጉዞ ገና ብዙ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
በመሆኑም ከተማዋን ወደ ላቀ ከፍታ ማማ ለመውሰድ በሚደረገው ጉዞ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም በነበረው ቁርጠኝነትና የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
“ይህንን ታላቅ በዓል ስናከብር እንደ ወትሮው ሁሉ የተራቡትን በማጉረስ፣ የታረዙትን በማልበስ እና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመደገፍ፣ ካለን ላይ በማካፈል የበዓሉን በረከት ልናበዛ ይገባል” ብለዋል።
በዕለቱም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የፈጣሪን ታላቅነት የሚያወድሱ (ተክቢራዎችን) በማሰማት በአሉ በሰላም ተጠናቋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
