“የምርጫው ቀን ሕዝባችን ያለምንም ስጋት ድምጽ የሚሰጥበት ታሪካዊ ቀን እንዲኾን እናደርጋለን” ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)

8

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሁናዊ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ እና ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የጠቅላይ መምሪያው አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) የክልሉ ሕዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም እንከን የሚፈልገውን የፖለቲካ ፖርቲ የሚመርጥበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ለዚህም የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል እና ክልል ፖሊስ፣ የክልሉ ሰላም አስከባሪ፣ ሚሊሻ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።

የምርጫ ጽሕፈት ቤት በተከፈቱባቸው እና ምርጫ ጣቢያ ባሉባቸው የክልሉ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ በድምጽ መስጫ ቀን በየትኛውም ሰዓት ወጥቶ በዕለቱ መምረጥ እንዲችል የተቀናጀ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስምሪት እንደተሰጠም አመላክተዋል።

“ዕለቱ ያለምንም ተጽዕኖ ሕዝባችን የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ የሚሰጥበት እና መንግሥት የሚመርጥበት ታሪካዊ ቀን እንዲኾን እናደርጋለንም” ብለዋል። አሁን ላይ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያሰጋ ሁኔታ እንደሌለ እና በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ማኅበረሰቡ የምርጫ ሂደቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጸጥታ ኃይሉን በማገዝ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰዋል። የማኅበረሰቡ ትብብር የሚመሰገን እና ትልቅ እውቅና የሚሰጠው እንደኾነ ነው የገለጹት።

በቀጣይም ይህን የነቃ ተሳትፎ በማጠናከር የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን ሲመለከት ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በስልክ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና በሞባይል አፕሊኬሽን (EFPApp) አማካኝነት መረጃ ለማድረስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ብለዋል።

በዚህም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩን ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ደሴ ከተማን ወደ ላቀ ከፍታ ማማ ለመውሰድ በሚደረገው ጉዞ ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ” አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሚኮ በደሴ ከተማ እያስገነባው የሚገኘውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎበኙ።