🕋ሃጅ እና ሃይማኖታዊ በረከቶቹ

8

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሃጅ በእስልምና ሃይማኖት ከአምስቱ የኢስላማዊ ግዴታዎች መካከል አንዱ ነው። አቅሙ የፈቀደ ሙስሊም ሁሉ በእድሜ ዘመኑ አንድ ጊዜ ሊያከናውነው የሚገባ ግዴታ ነው።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ ሙሐመድ ኢብራሂም እንደገለጹት አንድ ሰው ሃጅ ሲፈጽም አላህ የሰጠውን ግዴታ የተወጣ እና ከአላህ ዘንድ መቃረቢያም ይሆንለታል።

አንድ ሙስሊም የሃጅ ሥርዓትን ፈጽሞ ሲመጣ ልክ እናቱ እንደወለደችው ሕጻን ከወንጀል(ከፈጸመው ክፉ ነገር) ነጻ ኾኖ እንደሚመለስ የነቢዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ እየጠቀሱ ያብራራሉ።

ሐጂ በአላህ ዘንድ እጅግ የተከበረ እና ታላቅ መንፈሳዊ ጉዞ እንደመሆኑ መጠን ለአማኙ ዘርፈ ብዙ በረከቶችን ያስገኛል ነው ያሉት። ሼሕ ሙሐመድ ማብራሪያ ሃጅ መፈጸም :-

✅ከወንጀል(ከሀጢያት) መንጻት:-በሥርዓቱ መሠረት ሃጅን በጥሩ ሁኔታ የፈጸመ ሰው ልክ እናቱ እንደወለደችው ህፃን ከኃጢአት ንጹህ ሆኖ ይመለሳል።

✅የአንድነት እና የእኩልነት ስሜትን ይገነባል:-በሥርዓቱ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ነጭ ልብስ (ኢህራም) ለብሶ፣ የሃብት፣ የስልጣን እና የዘር ልዩነት ሳይደረግበት በአንድ አምላክ ፊት መቆሙ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን በተግባር እንዲረዳ ያደርጋል።

✅የአላህን ቅርበት እና ዝክር በልብ ውስጥ ያሰርጻል:- በተለያዩ ቅዱስ ስፍራዎች ዱዓ በማድረግ አማኙ ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት ይጠናክራል።

✅በተለይም በዓረፋ ተራራ ላይ መቆም የመጨረሻውን የፍርድ ቀን ስለሚያስታውስ ሰው ስለ ራሱ ሕይወት በጥልቀት እንዲያስብ እና ወደ ቀጥተኛው መንገድ እንዲመለስ ያነሳሳዋል።

✅ የሃጅ ጉዞ የሚጠይቀው ድካም፣ መስዋዕትነት እና ትዕግስት በሥነ ምግባር በመቅረጽ በኩል ከፍተኛ ሚና አለው። ይህም ከሃጅ መልስ ለሚኖረው ማህበራዊ መሥተጋብር ትልቅ ስንቅ ይኾነዋል።

✅ሃጅ የሃይማኖት መሰረት የሚያጸና፣ ልብን የሚያለሰልስ፣ ሰላምን እና መንፈሳዊ እርካታን የሚሰጥ ዘርፈ ብዙ በረከት እንዳለውም አብራርተዋል።

#አሚኮ #ሃጅ #እስልምና #አረፋ #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🕌 “ኢድ አል አደሃ (አረፋ) የመታዘዝ እና የመተሳሰብ ታላቅ መድረክ”
Next article“ከኢድ አል አደሃ (ከአረፋ) በዓል መታዘዝን እና ጽናትን መማር ይገባል” ሼህ ጀዋር ሙሐመድ