“ከኢድ አል አደሃ (ከአረፋ) በዓል መታዘዝን እና ጽናትን መማር ይገባል” ሼህ ጀዋር ሙሐመድ

5

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሼህ ጀዋር ሙሐመድ የባሕር ዳር መጅሊስ የሰበካ እና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ እንዲሁም የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ናቸው።

የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል መነሻው ነብዩ ኢብራሒም ልጃቸውን ነብዩ ኢስማኤልን ለመሰዋት የወሰኑበት ታላቅ ታሪክ ነው ይላሉ። ይህ የመስዋዕትነት መንፈሳዊ ታሪክ “ላመኑበት ነገር እስከ መጨረሻው መዝለቅን” በተግባር ያሳየናል ብለዋል።

ነብዩ ኢስማኤል“አባቴ ሆይ የታዘዝከውን ፈጽም፤ ከታጋሾች ታገኘኛለህ” በማለት የአባታቸውን ጥሪ የተቀበሉበት ንግግር ለፈጣሪ ፍጹም መታዘዝን፣ ፍቅር እና እምነትን ያሳያል ነው ያሉት።

በዚህ ዘመን ያለው ወጣትም ፈጣሪውን ከማክበር ባሻገር ለወላጆቹ፣ ለሀገሩ እና ለሞራል እሴቶች መታዘዝን ከዚህ ትምህርት ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ የአረፋ ታሪክ ሌላኛው ምሰሶ ነው የሚሉት ሼህ ጀዋር የአሁኑ ትውልድም በሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ፈተናዎች በጽናት እና በሰላም ለማለፍ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት መክረዋል።

የአረፋ በዓል ለላቀ ዓላማ የራስን ፍላጎት መስዋዕት ማድረግን ያስተምራል ብለዋል።

በመኾኑም ወጣቱ ለጊዜያዊ ጥቅም ከመታለል ተቆጥቦ ለሀገር እና ለወገን ጥቅም ሲባል ጊዜውን፣ ዕውቀቱን እና ጉልበቱን መስዋዕት በማድረግ ከኢብራሒም እና ከእስማኤል ቤተሰቦች መማር እንዳለበት አንስተዋል።

1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል የሰላም፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲኾንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🕋ሃጅ እና ሃይማኖታዊ በረከቶቹ
Next articleግጭት ያልበገረው ልማት በእስቴ ወረዳ።