ግጭት ያልበገረው ልማት በእስቴ ወረዳ።

5

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ካለው የትምህርት ፍላጎት አኳያ ያለው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሲታይ አነስተኛ እንደኾነ ይታመናል።ለዚህ ማሳያ የሚኾነው ደግሞ በየቀበሌው የሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መኾናቸው እና በወረዳው በቂ ሁለተኛ ደረጃ እና መሠናዶ ትምህር ቤት አለመኖራቸው ነው።

በአብዛኛው የወረዳው ቀበሌዎች የሚገኙ ተማሪዎች የሁለተኛና መሠናዶ ትምህርታቸውን በመካነ ኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር በሚገኘው እና በሌሎች ውስን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ረጅም እርቀት ተጉዘው ሲማሩ ቆይተዋል።

አሁን ላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን የእስቴ ወረዳ አሥተዳደር አስታውቋል።

በወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች 39 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የመማሪያ፣ አሥተዳደር እና መሰል ግንባታዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዱኛው ጎቤ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በ2017 ዓ.ም ተጀምረው በአጭር ጊዜ የተጠናቀቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የተገነቡት ሕንጻዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ምቹ በመኾናቸው የሕፃናትን የመማር ፍላጎት እንደሚጨምሩ እና የትምህርት ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩ ነው የተናገሩት።

የእስቴ ወረዳ አሥተዳዳሪ ማንተፋርዶ ሞላ ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት፣ በአማራ ልማት ማኅበር እና በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ መሆናቸውን አንስተዋል።

የተገነቡት ተቋማት የነገ ሀገር ተረካቢው ትውልድ የሚቀረጽባቸው ናቸው ያሉት አሥተዳዳሪው ማኅበረሰቡ በጥንቃቄ በመያዝ ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

እስቴ ወረዳ ተደጋጋሚ ግጭት የሚነሳበት እና በርካታ ጉዳቶችን ያስተናገደ አካባቢ መኾኑን ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ የወረዳው አሥተዳደር ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የተለያዩ የልማት ሥራዎች እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

​በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዦች፣ የእስቴ ወረዳ እና የመካነ ኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች፣ መምህራን እና የወላጅ መምህራን ህብረት አባላት መገኘታቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከኢድ አል አደሃ (ከአረፋ) በዓል መታዘዝን እና ጽናትን መማር ይገባል” ሼህ ጀዋር ሙሐመድ
Next articleወደ ፈጣሪ የሚቀራረቡባቸው የላቁት የዙልሂጃ ቀናት