ወደ ፈጣሪ የሚቀራረቡባቸው የላቁት የዙልሂጃ ቀናት

5

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል ዛሬ እየተከበረ ነው።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼኽ መሀመድ ኢብራሂም የዙልሂጃ አስሩ ቀናት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እጅግ የላቀ ስፍራ የሚሰጣቸው መኾኑን ገልጸዋል።

የዙልሂጃ ስምንተኛው ቀን የሐጅ ሥነ-ሥርዓት የሚከናወንበት እንደኾነ ገልጸዋል። ነብዩ መሀመድ አማኞች በእነዚህ ቀናት አምልኮታቸውን በጾም፣ በሰደቃና በደግ ሥራዎች በማጠናከር ወደ ፈጣሪያቸው ይበልጥ እንዲቃረቡ አዘዋል ነው ያሉት።

በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን ላይ የሚደረገው የፆም ሥነ ሥርዓት ያለፈውንና የሚመጣውን የሁለት ዓመት ወንጀል የሚያስተሰርይ እንደኾነም ገልጸዋል።

ለዚህም ሁሉም ሙስሊም ሊጾመው እንደሚገባ ይገደዳል። ነገር ግን በሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ያሉና በጉዞ ላይ የሚገኙ እንግዶች እየደከሙ በመኾናቸው መጾም እንደማይገደዱ ነው ያስታወቁት።

አላህ በቁርአኑ የእነዚህን አሥር ሌሊቶች ታላቅነትና ልዩ ክብር ለመግለጽ በእነርሱ ምሏል። ይህንንም ያደረገው የዓድ፣ የሰሙድ እና የፈርኦንን አምባገነን መንግሥታት ታሪክና የደረሰባቸውን ኪሳራ ባወሳበት የቁርአን ክፍል ላይ እንደኾነ ጠቁመዋል።

እንደ ሼኽ መሀመድ አማኞች በእነዚህ ቀናት አቅማቸው የፈቀደውን መልካም ሥራ ሁሉ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። ከተጠቀሱት በጎ ተግባራት መካከል ጾም መጾም፣ ካላቸው ላይ በማካፈል ደሃዎችን መርዳት፣ ቁርአን መቅራትና የሌሊት ጸሎት ማድረግ ይገኙበታል። በእነዚህ ቀናት የሚሠሩ መልካም ሥራዎች በጦር ሜዳ ጂሃድ ወጥቶ ከሚመለስ ሰው ጋር እንኳን የማይስተካከሉና ደረጃቸው እጅግ የላቀ መኾኑን ነብዩ መሀመድ አስተምረዋል።

ዘጋቢ: ስማቸው አጥናፍ

#አሚኮ #አረፋ #ዒድ_አል_አደሃ #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭት ያልበገረው ልማት በእስቴ ወረዳ።
Next articleየኢድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።