እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አል አድሐ በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ!

11
ስለዒድ አል-አድሐ “ዐረፋ” በዓል ስናስብ ሦስት ነገሮች ቀድመው ይታወሱናል። መስዕዋትነት፣ መታዘዝ እና መተጋገዝ። አባት ልጁን ለመስዕዋት ያቀረበበት፤ ልጅ የአባቱን ትዕዛዝ የፈጸመበት፤ ሙስሊሞች የመተጋገዝን እሴት ለዓለም የገለጡበት በዓል ስለሆነ “ዐረፋ” በሕዝበ-ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ትርጉም አለው።
እስማኤል ለነብዩ ኢብራሂም የመጀመሪያ እና ተወዳጅ ልጃቸው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ይሄን ተወዳጅና የመጀመሪያ ልጅ እንዲሠዉለት ሲጠይቃቸው ታዘዙ እንጂ ወደኋላ አላሉም። ለመታዘዝ የሞከሩት ነገሩ ቀላል ሆኖ አይደለም። ልጅን ያህል ነገር መስዕዋት ማድረግ ምኑ ይቀላል? የአባትነት ስሜት ይተናነቃል። የሰይጣን ሹክሹክታ ይፈታተናል። የቤተዘመድን ወቀሳ እና የጎረቤትን አስተያየት መቋቋምም ይከብዳል። ነብዩ ኢብራሒም፥ በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ አንድ ሐቅ ተገልጦላቸዋል። ከራስ ስሜት፣ ከሰው ሐሜት እና ከወዳጅ ፍላጎት የሚልቅ ታላቅ ዓላማ እንዳለ አምነዋል። ስለዚህም በፈተና ውስጥ ጸንተው ቆሙ፤ ቆራጥነታቸውም በተግባር ታየ።
ሀገር የምትገነባው ከራስ ጥቅም በላይ በሚያስቡ እና ከግላዊ ፍላጎታቸው በላይ ለመፈጸም በቆረጡ ዜጎች ነው። የሚወዱትን ነገር እንኳን ሳይቀር ለመሠዋት ዝግጁ የሆኑ ዜጎች ሲበዙላት ሀገር ትበረታለች። እስማኤላቸውን ለመስጠት የማያመነቱ ዜጎች የሞሉባት ሀገር ጽኑ ናት።
የለመድናቸው፣ የምንወዳቸው፣ የራሳችን ገንዘብ ያደረግናቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ የሚበልጥ ዓላማ ግን አለ፤ እሱም “ሀገርነት እና ሉአላዊነት” ይሰኛል። ሀገርነት የሚገነባው ከመውሰድ ይልቅ በመስጠት ነው። ሉአላዊነት የሚጸናው በፈተና ሳይወድቁ በመቆም፤ በወጀብ ሳይናወጡ መጓዝ በመቻል ነው።
የእውነት ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ማየት የምንሻ ከሆነ ምኞታችን በተግባር ይገለጥ። የሀገር ኩስመና ካሳሰበን ለግዝፈቷ እንድከም። ያጎበጣትን የድህነት ቋጥኝ ለመሸከም ትከሻችንን እናመቻች። ጎተራዋ እንዲሞላ እጃችን አፈር ይንካ። የጠየመ ገጽዋ እንዲፈካ በሥራ ሌት-ተቀን እንሰለፍ። የተቀማ ክብሯ እስኪመለስ ድርሻችንን እንወጣ። ሀገር መውደዳችን ከልብ ከሆነ መስዕዋት ለመሆን አናመንታ።
የዐረፋ በዓል የመታዘዝና የመስዕዋት ብቻ ሳይሆን የመደጋገፍና የመተጋገዝ በዓል ጭምር ነው። በዐረፋ ከሚከናወነው እርድ አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች እንዲሰጥ የእስልምና አስተምህሮ ያዛል። በዐረፋ ሕዝበ-ሙስሊሙ ደስታና ሐዘኑን እየተጋራ በዓሉን ያከብራል። የዐረፋ እለት አንድም ሰው ተከፍቶ አያሳልፍም፤ በዐረፋ ሰሞን ማንም ሰው ተርቦና ተጠምቶ አያድርም። በዓሉ ትርጉም የሚሰጠው ሕዝበ-ሙስሊሙ ያለውን ተካፍሎ ሲያከብረው ነው። ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚሻገሩበት መፍትሄው መተሳሰብና መተጋገዝ እንደሆነ ከዐረፋ እንማራለን። ሀገርም ከፈተናዎችዋ በላይ እንድትሆን እኒህ እሴቶች ወሳኝ ናቸው።
ዐረፋ ማኅበረሰባዊ በዓል የሚባለው ለዚህ ነው። ሰዎች በግላቸው የሚያከብሩት አይደለም። ቤተሰቡ፣ ጎረቤቱ፣ ሠፈሩ፣ ከተማው የሚያከብረው በዓል ነው። ያላቸውና የሌላቸው፤ የሚችሉና የማይችሉ፤ ታላላቆችና ታናናሾች፤ ባለ ሥልጣናትና ተራ ዜጎች፣ በአንድነት የሚያከብሩት በዓል ነው። ሰው የሚኖረው በቤቱ ውስጥ አይደለም። በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው።
ማኅበረሰባዊ ትሥሥርና ትብብር ለዜጎች እና ለሀገር ደኅንነት ወሳኝ ናቸው። ማኅበረሰባዊ ትሥሥር ስለሌሎች እንድናስብ፣ ስለሌሎች እንድንሠራ እና ስለ ሌሎች ዋጋ እንድንከፍል ያደርገናል። ራሳችንን በሌሎች ጫማ ላይ አቁመን እንድናይ ያስችለናል። የሁላችንም ሰላም፣ የሁላችንም ደኅንነት እና የሁላችንም ጥቅም ካልተከበረ በቀር የግላችንን ብቻ ልናስከብር እንደማንችል ያስገነዝበናል። ስለዚህም ማኅበራዊ ግዴታን እንደ ዜግነት ግዴታ ወስደን እንድንሠራ ያደርገናል።
ምርጫ ማኅበራዊና ዜግነታዊ ግዴታዎችን ከምንወጣባቸው የዴሞክራሲ መገንቢያ መሳሪያዎች መካከል ዋነኛው ነው። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲ አይሳካም። ያለ ምርጫም የሕዝብ ተሳትፎ ምሉዕ አይሆንም። የዴሞክራሲያችን መሰረት ጥንካሬው የሚለካው በተሳትፎአችን መጠን ነው።
የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሀገረ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን የሚጠነክርበት መሰረት ነው። የዴሞክራሲ ልምምዳችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚልበት፤ የቀጣይ ዓመታት የሀገራችንን እጣ-ፈንታ የምንበይንበት፤ ከምንም በላይ ብዝሃ-ድምጽ የሚሰማበት የሕግ መወሰኛ ምክርቤት የምንመሰርትበት ወሳኝ አጋጣሚ ነው። በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ዜግነታዊ ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን በካርዳችን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለማረጋገጥ እየተዘጋጀን እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ!
ዒድ ሙባረክ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ግንቦት 18፣ 2018 ዓ.ም
Previous articleየአማራ ክልል የፍርድ ቤቶች ጥሪ ማዕከል በሙሉ አቅሙ ሥራ ጀመረ።
Next article“ከግንቦት 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ የጥሞና ጊዜ ነው” ምርጫ ቦርድ