
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጎንደር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስጀምረዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ማዕከላዊ ጎንደር የብዙ ጸጋዎች ያሉት አካባቢ መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ባለው ጸጋ ልክ ሳይለማ መቆየቱን ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት ኢንዱስትሪዎች መገንባት የአካባቢውን ጸጋ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ የእድገት ተስፋ መኾኑን አንስተዋል። በቀጣናው የኢኮኖሚ መነቃቃትን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
ለቀጣናው የግብርና ምርት እድገት ትልቅ አቅም እንደሚኾንም ተናግረዋል። ኢንዱስትሪው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲኾን ለክልሉ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚሆን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ጣምያለው የአምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረው ሚና ታላቅ መኾኑን ገልጸዋል።
የጎንደር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም እንደሚኾን ገልጸዋል። የፓርኩ ግንባታ የሚካሄድበትን ሥፍራ ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ለማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እና ግብርናውን የሚያዘምን ነው ብለዋል። ፓርኩ በውስጡ በርካታ አቅሞችንም የያዘ መኾኑን አስረድተዋል።
ፓርኩን በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት ለማጠናቀቅ ይሠራል ነው ያሉት። የፓርኩ ወደ ግንባታ እንዲገባ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
