“ኢንዱስትሪ ፓርኩ የቀጣናው የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

5

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጎንደር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን አስጀምረዋል።

በግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዛሬ ያስጀመርነው የጎንደር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ከያዝናቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል አንደኛው ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት አልሞ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ሽግግሩን ለማሳለጥ የሚለማውን ሃብት መለየት እና አልሚ ባለሃብቶችን የሚያቆራኘውን መሠረተ ልማት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ፓርኩ የሰሜን ምዕራብ የልማት የስበት ማዕከል መኾኑን ተናግረዋል። በቀጣናው ያለውን ሃብት እና ጸጋ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል። ቀጣናው በሀገር ደረጃ ከፍተኛ አቅም ያለው የቅባት እህል የሚመረትበት መኾኑን አንስተዋል።

ወደ ውጭ የሚወጣው አብዛኛው የቅባት እህል የሚመረተው በዚሁ ቀጣና ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ እስካሁን ወደ ውጭ የሚቀርበው እሴት ሳይጨምርበት ነው፤ ይህ ደግሞ በልካችን እንዳንጠቀም አድርጎን ቆይቷል ብለዋል።

ፓርኩ እሴት ጨምሮ ወደ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል። አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲኾኑ እና የማምረት ልምዳቸውን እንዲቀይሩ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ የኢኮኖሚ ሽግግርን የሚያረጋግጥ፤ ባለሀብቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው ብለዋል። በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአካባቢው መሪዎች ፕሮጄክቱን በየጊዜው እንዲከታተሉ አሳስበዋል። በአካባቢው ትርፋማ ምርት እንዲመረት በትኩረት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። ልማትን ለማረጋገጥ ሰላምን መጠበቅ እና ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። ፕሮጄክቱን የያዙት የልማት ድርጅቶችም ሥራውን በፍጥነት እንዲሠሩ አስገንዝበዋል።

ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ትርፍ በማምረት እና አቅምን በማሳደግ ነው ብለዋል። የመጣውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

#አሚኮ #ጎንደር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleምርጫን ማካሄድ ሰላምን እና ልማትን ማጽናት ነው።
Next articleኢንዱስትሪ ፓርኩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሰላምን መጠበቅ ይገባል” አቶ መላኩ አለበል