
ሰቆጣ: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 30ኛ ዓመት የሚሊሻ የምሥረታ በዓል በሰቆጣ ከተማ በተለያዩ ኹነቶች ተከብሯል።
ባለፉት 30 ዓመታት ለሀገር ሰላም መጽናት የተከፈለው መስዋዕትነት ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ጀብድ እንደነበር ያነሱት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ 50 አለቃ አዘዘው አዳነ ናቸው።
ሀገራችን የምታካሂደውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የጸጥታ መዋቅሩ ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም በምርጫ ሂደቱ የላቀ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ የሚሊሻ አባላት የአካባቢን ሰላም ከመጠበቅ አልፎ የሀገርን ዳር ድንበር የመጠበቅ አቅም ያላቸው የሰላም አምባሳደር ናቸው ብለዋል።
ሚሊሻ ደሳለኝ ጸጋው እና ሚሊሻ ጥጋቡ መኳንንቴ የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በትጋት የሠሩ ተሸላሚ ሲኾኑ የዋግ ኽምራን ሰላም አጽንተው ለማስቀጠል ቁርጠኛ እንደኾኑ ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሕዝባቸው ጋር በትጋት እንደሚሠሩ ነው የገለጹት።
በምስረታ በዓሉ ላይ የተገኙ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የአካባቢውን ሰላም በማጽናት ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን ኾነው እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
