
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአርጎባ አንድነት ጀበርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። በስብሰባው ላይም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራት እና የፓርቲ ሥራዎችን በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው መረጃ ጠቁሟል።
በምርጫው ዕለት እና ድህረ ምርጫ ሁኔታዎችን በመገምገም ከፓርቲው የሚጠበቀውን ኀላፊነት ለመወጣት ወስነናል ነው ያለው ኮሚቴው።
የእጩዎች ምዝገባ በቴክኖሎጂ መኾኑ አሠራሩ የመጀመሪያ ቢኾንም ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር የተሻለ ነው፤ የፓርቲው 177 እጩዎች የተመዘገቡ ሲሆን በሲስተም ችግር ያልተመዘገበ እጩም የለንም ብለዋል። የእጩዎች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን በመጥቀስ ለዚህም የምርጫ ቦርዱን ባለሙያዎችና አመራሮች ድጋፋቸው የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተሻለ የመራጮች መዝገባ መካሄዱን እና ፓርቲው ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል። በቀሪ ጊዜያት የበለጠ ቅስቀሳ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ምደባ በማድረግ ቅስቀሳው እንዲካሄድ ለፓርቲው አመራሮች በተለዩ ዞኖች ምደባ ስለመደረጉም ተመላክቷል፡፡
የባሕር በር፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ፓርቲው ከመንግሥት ጎን በመቆም ድጋፍ የሚያደርግባቸው እና በትኩረት የሚሠራባቸው ጉዳዮች ስለመኾናቸውም የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ በመግለጫው አረጋግጧል።
“7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፓርቲው የሚጠበቀውን ኀላፊነት ለመወጣት ወስነናል” ሲልም መግለጫው አካትቷል።
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
