“ብልጽግና የ30 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባ ፓርቲ ነው” የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም

6

 

ደሴ፡ ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ እና የምረጡኝ ቅስቀሳ በደቡብ ወሎ ዞን ጊምባ ከተማ ተካሂዷል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጊምባ ከተማ ብልጽና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በሽር ቦጋለ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነት የሚያገለግል፣ ዘርፈ ብዙ ስብራቶችን በመጠገን ብዝኀነትን የሚያከብር ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መኾኑን ተናግረዋል።

የጊምባ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እያሱ ዓባይ ብልጽግና ባለፋት ዓመታት በርካታ ስኬቶች ያስመዘገበ ፓርቲ መኾኑን አንስተዋል። የሕዳሴ ግድብን ከውስብስብ ችግር አውጥቶ ለፍጻሜ ያበቃና የቀጣናውን ጂኦ ፖለቲካዊ ስትራቴጂ አቅጣጫ ያስተካከለ ፓርቲ መኾኑንም ገልጸዋል።

ፓርቲው ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ያሉት ከንቲባው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ብልጽግናን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ፣ የልጆቻችንን መጻኢ ዕድል እና የሀገራችንን ሰላም እና ልማት የምንወስንበት የታሪክ ምዕራፍ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ናቸው።
ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ኀላፊነት ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በተጨባጭ ፍሬዎች ሀገራችንን መርቷል ነው ያሉት።

ብልጽግና ፓርቲ በልማትና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይኾን፣ የሀገርን ህልውና በማስከበር እና የሕዝብን አንድነት በመገንባት ረገድ መስዋዕትነት የከፈለና ታሪካዊ ድሎች ያሉት ፓርቲ መኾኑንም ምክትል ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግሥት ከኾነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የ30 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶች እቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን ነው አቶ አሊ የገለጹት።

የብልጽግና ፓርቲ በጦርነት እሳት ውስጥ አልፎ፣ የውጭ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ፣ የዜጎችን ክብር ጠብቆ ሀገርን ያሻገረ ፓርቲ ነውም ብለዋል ።

“በሰባተኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ድምፃችሁን ለብልጽግና ፓርቲ በመስጠት የሀገራችሁን ሉዓላዊነት እና ክብር እንድታስጠብቁ እና እንድታፀኑ እጠይቃለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።

በምርጫ መንግሥት ለማቋቋም ዕለቱን እየተጠባበቁ መኾኑን የተናገሩት የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በካርዳቸው ይበጀናል ያሉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ።