
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልልን የትምህርት ቤቶች ደረጃ በማሻሻል የትምህርትን ተሳትፎ ከጥራት ጋር ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። በዚህ ረገድ የሰሜን ሸዋ ዞን ተጠቃሽ ነው።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጸጋዬ እንግዳወርቅ የሰላም እጦትን ተከትሎ በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ ከማስተካከል ጀምሮ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በበበጀት ዓመቱ ከ2 ቢሊዮን 634 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የትምህርት ቤቶች ግንባታ በመከናወን ላይ መኾኑንም አንስተዋል።
ይህም የመማሪያ ክፍሎችን እጥረት ለመፍታት እና ምቹ የትምህርት አካባቢን ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
👉 በዞኑ በቅድመ አንደኛ የትምህርት ደረጃ 23 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
👉 በትምህርት ሚኒስቴር እና በወረዳ ማቺንግ ፈንድ ውል ተይዞላቸው በግንባታ ላይ ለሚገኙ 49 የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ545 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ እየተሠራ ነው ብለዋል ኀላፊው።
👉 በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተራድኦ ድርጅቶች፤ በአማራ ልማት ማኅበር እና በመንግሥት በጀት 588 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታቸው ተጠናቅቋል ነው ያሉት። ተጨማሪ 52 የመማሪያ ክፍሎች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት።
👉 ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ማስፋፊያ በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን 394 ሚሊየን ብር ሥራ ላይ ውሏል።
👉 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማሳደግ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በአልማ እና በካፒታል ፕሮጀክቶች የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ለዚህም 694 ሚሊዮን 545 ሺህ 838 ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።
በሁሉም የትምህርት እርከኖች አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ለ2019 የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንዲኾኑ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
