
ባሕር ዳር: ግንቦት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ለብዙዎች የፖለቲካ ክንውን ብቻ ሊኾን ይችላል። በአለፋ ወረዳ ሻሁራ ከተማ ነዋሪ ለኾኑት ለወይዘሮ አበቄ አልጋው ግን የህልውና እና የነገ ተስፋ ጉዳይ ነው።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ በቀዳሚነት የወሰዱት ወይዘሮ አበቄ ካርዳቸውን በእጃቸው ሲጨብጡ የሚሰማቸው ስሜት የተለየ ነው።
“ይህች የያዝኳት የምርጫ ካርድ ተራ ወረቀት አይደለችም፤ የነገ ሕይወቴን የምወስንባት ትልቁ መሣሪያዬ ናት” ይላሉ በኩራት።
የእሳቸው የዴሞክራሲ ተሳትፎ በግል ብቻ የተወሰነ አይደለም። የእናትነት አርዓያነታቸውን በመጠቀም አምስት የቤተሰባቸው አባላትም ካርድ እንዲያወጡ አድርገዋል።
ወይዘሮ አበቄን ለየት የሚያደርጋቸው ትልቅ ታሪክ አላቸው። ይኸውም ላለፉት ተከታታይ ሰባት የምርጫ ሂደቶች ያለምንም ማቋረጥ ድምፃቸውን ሲሰጡ መቆየታቸው ነው። ባለፉት ስድስት የምርጫ ጊዜያት ያለምንም ጫና እና ግፊት ውስጣቸው ያመነበትን እና ያስተዳድረኛል ያሉትን ፓርቲ በሙሉ ነፃነት መምረጣቸውን ያስታውሳሉ።
ዛሬም የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታሪክ አካል ለመኾን ካርዳቸውን ቀድመው ይዘዋል። ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ለዜጎች ሰላም መከበር የተሻለ አማራጭ ይዞ የመጣውን ፓርቲ ለመምረጥም ቀናትን እየቆጠሩ ነው።
ለዚህም ነው አሁን ላይ ግንቦት 24/2018 ዓ.ምን ልክ እንደ ትልቅ በዓል በጉጉት እና በናፍቆት እየጠበቁ ያሉት። ምርጫው ሰላማዊ እና ትክክለኛ እንዲኾንም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የወይዘሮ አበቄን የአርዓያነት ፈለግ የምትከተለው ደግሞ በዚሁ ከተማ የምትኖረው ወጣት መሠረት አለሰው ናት። ወጣት መሠረትም ልክ እንደ አዛውንቷ እናት የምርጫ ካርዷን ቀድማ በእጇ አስገብታለች።
“በምርጫ ሂደት ውስጥ የሴቶች የነቃ ተሳትፎ መኖር የነገዋን ሀገር መልክ ይወስናል” የምትለው ወጣት መሠረት ዘንድሮ ከመምረጥም ባለፈ አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ሄዳለች። በምርጫ ታዛቢነትም ተመልምላ የምርጫ ሂደቱን በታማኝነት ለማገልገል ሌት ተቀን እየሠራችም ትገኛለች።
የሻሁራ ከተማ የምርጫ ድባብ በዕድሜ ጠገቧ ወይዘሮ አበቄ የጽናት ጉዞ እና በወጣት መሠረት ንቁ ተሳትፎ ደምቋል። የነገዋን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ሁለቱም ትውልዶች በአንድ ዓላማ ቆመው የምርጫዋን ቀን በናፍቆት እየጠበቁ ነው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #ምዕራብ_ጎንደር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
