“የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ የኖረው በጸጥታ ኃይሉ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

5

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሰርቲፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን መኮንኖች አስመርቋል።

ሠልጣኞች በወንጀል መከላከል፤ በወንጀል ምርመራ፤ በፎረንሲክ ምርመራ፤ በጤና፤ በፖሊስ ሳይንስ እና በሌሎች ዘርፎች የሠለጠኑ ናቸው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል እና ቀጣናዊ ሰላምን ለማስከበር በዕውቀት እና በሳይንሳዊ ትንተና ላይ ተመስርቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ይህንን ለማሳካት በሰው ኃይል ሥልጠና ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሥልጠና ያጠናቀቁ ተማሪዎች የሪፎረሙ አካል ናቸው ብለዋል።

ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ከጎረቤት ሀገራት ለመጡ ሠልጣኞች ነጻ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው መመረቃቸውንም አስታውቀዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የፌዴራል ፖሊስ በሰው ኃይል፣ በትጥቅ እና በቴክኖሎጅ አቅሙን እያጠናከረ መኾኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችም የታጠቁትን ዕውቀት እና ቴክኖሎጅ ተጠቅመው ሀገርን ከጠላት ለመጠበቅ እንዲተጉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ የኖረው በጸጥታ ኃይሉ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት በመኾኑ በአባቶቻችን ተከብሮ የኖረውን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል የጸጥታ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ተመራቂ የጸጥታ አካላት ከሚቀርቡላቸው ማንኛውም መደለያዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ሕዝባቸውን በታማኝነት እና በቅንነት እንዲያገለግሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ገለልተኛ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት ምቹ እና አስተማማኝ የሰላም አካባቢ እንዲፈጠር በትጋት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ምርጫው ለሕዝባዊ የልማት ተጠቃሚነት መሠረት የሚጥል ነው” ስቡሕ ገበያው (ዶ.ር)