“ምርጫው ለሕዝባዊ የልማት ተጠቃሚነት መሠረት የሚጥል ነው” ስቡሕ ገበያው (ዶ.ር)

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የባለፉት የለውጥ ዓመታት ልማታዊ ጉዞን የሚደግፍ ሰልፍ እና የምርጫ ቅስቀሳ ተካሂዷል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጌትነት እሸቱ
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ብልጽግናን መምረጥ የበለጸገች ኢትዮጵያን መምረጥ ነው ብለዋል።

ፓርቲው ወደ ሁለንተናዊ ልዕልና መሸጋገሪያ ምዕራፍ እንደኾነም ገልጸዋል። የበለጸገች ኢትዮጵያን ማፅናት እንደሚገባም አንስተዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ፈንታይቱ ካሴ ብልጽግና ፓርቲ ከተስፋ ቃል ገቢራዊ ልማትን ያረጋገጠ ፓርቲ ነው ብለዋል። በበጋ መስኖ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተግባራዊ የሚኾኑ ልማቶች የሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብርም ተጨባጭ ልማቶች አየተከናወኑ መኾናቸውን አንስተዋል። እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፌዴራል እና በክልል መንግሥት ለትውልድ የሚተርፉ ልማቶች መተግበራቸውንም አብራርተዋል።

የብሔረሰቡን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ የሚያደርጉ በክልሉ መንግሥት የሚገነባው የአልዋቅ የጫጩት ማሥፈልፈያ ግንባታ እና የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት በምሣሌነት የሚጠቀሱ እንደኾኑም ተናግረዋል።

በውኃ፣ በቴሌ፣ በመንገድ እና በመብራት መሠረት ተደራሽነት ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል። በጤናው ዘርፍ ከ30 በላይ የሚኾኑ የጤና ሥርዓቱን የሚያሣልጡ ጤና ተቋማት መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ እና የማሥፋፊያ ግንባታ ሥራዎች በሞዴልነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ስቡሕ ገበያው (ዶ.ር) ኢትዮጵያን ካጸኑ ሕዝቦች መካከል የአገው ሕዝብ አንዱ ነው ብለዋል። ዋግኽምራ በሰላም እና ልማት ወዳድነቱ ዓረዓያ የሚኾን ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ መኾኑን ገልጸዋል።

የብሔረሰቡ ሕዝብ ባለፉት 30 ዓመታት እምበዛም የልማት ተጠቃሚ እንዳልነበረ ያስታወሱት ኀላፊው የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

ምርጫው ለሕዝባዊ የልማት ተጠቃሚነት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል። የልማት ተጠቃሚነትን ማሥቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት 🏭 ብልጽግና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ የኖረው በጸጥታ ኃይሉ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ