
ደሴ፡ ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ብልጽግና ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትኾን እየሠራ ነው ብለዋል።
በስንዴ ልማት ራስን በመቻል፣ የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ እና በሌሎች ልማቶች ብልጽግና እንደ ሀገር ቃል የገባቸውን መፈጸም እንደቻለ አንስተዋል። ሰላም እንዲጸና እና ልማት እንዲሳለጥ ብልጽግናን መምረጥ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ብልጽግና ሕጋዊ እና ሕዝባዊ መንግሥት የሚመሠረተው በምርጫ ነው ብሎ ያምናል ብለዋል።
በካርዳችሁ ብልጽግናን በመምረጥ ሕጋዊ መንግሥትን ልትመሠርቱ ይገባልም ነው ያሉት።
የጸና ሰላም እንዲረጋገጥ ብልጽግናን መምረጥ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግሥት ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ ድጎማ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ብልጽግና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚ ለማድረግ ብልጽግና እየሠራ በመኾኑ ብልጽግናን ምረጡ ነው ያሉት።
ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ብልጽግና በትኩረት እየሠራ መኾኑን አንስተው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በካርዳቸው ብልጽግናን እንዲመርጡ አሳስበዋል።
የአካባቢውን ማኅበረሰብ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ጠቅላላምርጫ #ደቡብወሎ_ወግዲ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
